+ All Categories
Home > Documents > ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር...

ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር...

Date post: 14-Mar-2020
Category:
Upload: others
View: 33 times
Download: 6 times
Share this document with a friend
14
1 ቁጥር - ጥቅምት ፪ሺዓመተ ምሕረት የዕዝራ ስነ ጽሑፍ አገልግሎት ግብና ዓላማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትና ይዘት ያላቸውን ቅዱሳንን የሚመግቡ ከአጫጭር መጣጥፎች እስከ ትልልቅ የማስተማሪያ መርጃዎች በማዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንን መደገፍና በዚህም እግዚአብሔርን ማክበር ነው። ጥቅምት ፪ሺህ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 [email protected] ሰላምና ጸጋ ይብዛላችሁ፤ በዚህ ስርጭት ባለፉት የዕዝራ ስርጭቶች ከአንባቢዎች የተላኩልኝን ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን አያይዤ ለማቅረብ እያሰናዳሁ ሳለሁ በጎን ለምን እንደማሔስ አልፎ አልፎ እጠየቃለሁና ለምን እንደማሔስ ለመመለስ አጭር ጽሑፍ ጀመርኩ። ጽሑፉ ተለቀ፤ በጣም። ብቻውን ልልክ ያሰብኩትን የገጽ መጠን ሞላው። ጥያቄዎቹን በቀጣዩ ለማውጣት ተውኩት ማለት ነው። እስላምና ክርስትናም ፊልጵስዩስም በቀጣዮቹ ይከተላሉ። ለምን እንደማሔስ ልክ እንደ ርእሱ ለምን እንደማሔስ የጻፍኩበት ነው። ማሔስ ቀላል ነገር አይደለም። ለለመዱትና ግዴታ ለሚሰማቸው ካልሆነ በቀር የሚጥምም አይደለም። ለብዙዎች ጎምዛዛና መራራ ነው። ለለመዱት ግን ጣፋጭ ነው። ተጠያቂነትና ተፈታሽነት አንዳንዶችን ያስደነግጣል፤ አንዳንዶችን ያስፈገፍጋል። አንዳንዶችንም ያስቆጣል። ይሁን እንጂ ጥቂት ያልሆኑ ጉዳዮች መጥጠይቅ አለባቸው። መፍፈተሽና መገለጥም አለባቸው። 'ፈጣን ሎተሪ' እንደሚሉት ያለ ወዲያው ተጭሮ እንደሚያገኙት ባለ ቁማር ውስጥ ገብተው ለማያረካ ሕይወት የተዳረጉ ክርስቲያኖች ቁጥርም የዋዛ አይደለም። ክርስትና ክርስቶስን መምሰል እንጂ ብዙ ጊዜ ተበልተን አንዴ የምንበላው ቶምቦላ አይደለም። የሐሰት ትምህርቶችና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አፍንጫችን ተይዞ የምንጋታቸው የስሕተት ልምምዶች ዛሬም አያሌ ናቸው። እና ለምን እንደማሔስ ተረዱልኝ። መልካም ንባብ። ዘላለም መንግሥቱ / ዕዝራ ስነ ጽሑፍ። ቁጥር
Transcript
Page 1: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

1

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ለ ለ ም ን ን

እ ን ደ ማ ሔ ስ

የዕዝራ ስነ ጽሑፍ አገልግሎት ግብና ዓላማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትና ይዘት ያላቸውን ቅዱሳንን የሚመግቡ ከአጫጭር መጣጥፎች እስከ ትልልቅ የማስተማሪያ መርጃዎች በማዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንን መደገፍና በዚህም እግዚአብሔርን ማክበር ነው።

ጥቅምት ፪ሺህ ፯ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

[email protected]

ሰላምና ጸጋ ይብዛላችሁ፤

በዚህ ስርጭት ባለፉት የዕዝራ ስርጭቶች ከአንባቢዎች የተላኩልኝን ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን አያይዤ ለማቅረብ እያሰናዳሁ ሳለሁ በጎን ለምን እንደማሔስ አልፎ አልፎ እጠየቃለሁና ለምን እንደማሔስ ለመመለስ አጭር ጽሑፍ ጀመርኩ። ጽሑፉ ተለቀ፤ በጣም። ብቻውን ልልክ ያሰብኩትን የገጽ መጠን ሞላው። ጥያቄዎቹን በቀጣዩ ለማውጣት ተውኩት ማለት ነው። እስላምና ክርስትናም ፊልጵስዩስም በቀጣዮቹ ይከተላሉ።

ለምን እንደማሔስ ልክ እንደ ርእሱ ለምን እንደማሔስ የጻፍኩበት ነው። ማሔስ ቀላል ነገር አይደለም። ለለመዱትና ግዴታ ለሚሰማቸው ካልሆነ በቀር የሚጥምም አይደለም። ለብዙዎች ጎምዛዛና መራራ ነው። ለለመዱት ግን ጣፋጭ ነው። ተጠያቂነትና ተፈታሽነት አንዳንዶችን ያስደነግጣል፤ አንዳንዶችን ያስፈገፍጋል። አንዳንዶችንም ያስቆጣል። ይሁን እንጂ ጥቂት ያልሆኑ ጉዳዮች መጥጠይቅ አለባቸው። መፍፈተሽና መገለጥም አለባቸው።

'ፈጣን ሎተሪ' እንደሚሉት ያለ ወዲያው ተጭሮ እንደሚያገኙት ባለ ቁማር ውስጥ ገብተው ለማያረካ ሕይወት የተዳረጉ ክርስቲያኖች ቁጥርም የዋዛ አይደለም። ክርስትና ክርስቶስን መምሰል እንጂ ብዙ ጊዜ ተበልተን አንዴ የምንበላው ቶምቦላ አይደለም። የሐሰት ትምህርቶችና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አፍንጫችን ተይዞ የምንጋታቸው የስሕተት ልምምዶች ዛሬም አያሌ ናቸው። እና ለምን እንደማሔስ ተረዱልኝ።

መልካም ንባብ።

ዘላለም መንግሥቱ / ዕዝራ ስነ ጽሑፍ።

ቁጥር ፳፯

Page 2: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

2

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

(ሳንሱር፥ ሒስ እና እኔ) በቅርብም ሆነ በጽሑፎቼ የሚያውቁኝ ከሕያሴ ጋርር ስላለኝ ጥብቅ ትስስር ያውቃሉ። መንፈስ ቅዱስና ካሪዝማዊ ቀውሶች የተባለው መጽሐፌ ከታተመበት ዓመት (ከ18 ዓመታት በፊት) ጀምሮ እና አሁንም በዕዝራ ስርጭቶች እንደምጽፋቸው ያሉ የስሕተት ጥቆማና አመልካች ነገሮችን ለምን እንደማደርግ፥ ለምን ስሕተቶች ላይ እያነጣጠርኩ እንደምናገር ወይም እንደምጽፍና እንደምነቅፍ (አንዳንዶች ስሕተት መለቃቀም ብለውታል፤ አባባላቸው አሉታዊ ሆነ እንጂ ትርጉሙ ግን ትክክል ነው)፥ ለምን እንደማሔስ ይጠይቁኛል። ደፍረውና ቀርበው የሚጠይቁትን ማለቴ ነው። የማይጠይቁማ ያወራሉ፤ በግልጽ ያይደለ ይተቻሉ እንጂ አይጠይቁም። አንዳንዶቹም ያስጠነቅቁኛል፤ ለማስፈራራትም ይሞክራሉ። በዚህ ስርጭት ይህንን ነው የምጽፈው። ለምን እንደማሔስ። (ለምን critique እንደማደርግ።) እና ሌሎችም እንዲያደርጉ ለማበረታታት። ስለ ነገረ ሒስም ጥቂት እዚህ ጥቂት እዚያ እላለሁ። ገና ከጅምሩ ሁለት ነገሮችን በአጭሩ ልበል።

አንደኛው፥ ይህ መጣጥፍ ከግል ልምምዶች / ገጠመኞች ጋር የተለወሰ መሆኑን እናገራለሁ። አንዴ ወደ ፊት፥ አንዴ ወደ ኋላ እያልኩም እመላለሳለሁ። በዚህ ጽሑፍ ስለ ሒስ ብቻ ሳይሆን ስለ ራሴም 'ሒሳዊ' ልምምዶች በጥቂት እናገራለሁ ማለት ነው። እና እስካሁን ከምጽፈው መልክ በመጠኑ የተለየ ነው።

ሁለተኛው፥ ከላይ፥ 'ሌሎችም እንዲያደርጉ ለማበረታታት' ባልኩት ላይ ለማከል ነው። ይህ የሕያሴ (critique) ሥራ ፈሪ ልብ ላላቸው የማይመች መሆኑን አረጋግጣለሁ። ለአመቻማቾች አይስማማም። ለሕዝብ ሰዎች አይጥምምም። ዝናና ታዋቂነትን ለሚፈልጉ ከቶም መስካቸው አይደለም። ከስሕተት ልምምድና ከሐሰት ትምህርቶች ጋር ስትጋፈጡ ከስሕተተኞችና ከሐሰተኞች ጋር ግንባር ለግንባር ትጋጫላችሁ። አንዳንዶቹ ሳያውቁ የሚያጠፉ ናቸው። ካለመምማር፥ (ስጽፍ የሚጠብቁ ፊደላትን፥ 'ይህ ይጠብቃል' ከማለት ይልቅ በአንዳንድ ቋንቋዎች እንደሚደረገው ፊደላትን መደረብ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ) ካለማስተዋል፥ ከመኮረጅ፥ ከግድ የለሽነት፥ ወይም የሚያውቁት ልምምድ ያ ብቻ ከመሆኑ የተነሣ ከገቡበት እሽክርክሪት መውጣት ስለሚያቅታቸው፥ ከሰይጣን ሰለባነት የሚያጠፉ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ አውቀው ያጠፋሉ፤ አንዳንዶች ከጥቅም ጋር ይቆራኛሉ። በተለይ እነዚህ ስሕተታቸው ሲነገራቸው በቁጣ መጦፍና አንዳንዴም መፈንዳት ይታይባቸዋል። ፍንዳታው ሐያሲዎችንም ያቆስላል። ስለዚህ ቀላል ሥራ አይደለም። እመኑኝ፤ ሐያሲዎች ስማቸው ተሽሞንሙኖ አይነሣም። ከብዕር ስም በስተ ጀርባም አይደበቁም። መደበቅ አይችሉም፤ መደበቅም የለባቸውም። ሕያሴ የጊዜ፥ የአእምሮ፥ የስሜት፥ የንባብ ዋጋ ይጠይቃል። ነገሩ ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ከሆነ ደግሞ ቃሉንም ማጥናትን ይጠይቃል።

አሂዶና የውስጥ ፍተሻ 'ሒስ ወይም ማሔስ ምንድር ነው?' ብዬ ልጀምር። በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ ከሄድን ጥሬ ትርጉሙ ሒስ ወይም ሐስዮት፥ በደል፥ ገመና፥ የሚያስነቅፍ ነገር፥ ነቀፋ ማለት ነው። ሐያሲም ነቃፊ፥ ከሳሽ፥ ወቃሽ ማለት ነው። ሌላው ትርጉሙ ማሸት፥ ማፍተልተል፥ ማበራየት፥ መርገጥ፥ ማልፋት፥ ማፍረጥረጥ ማለት ነው። ደግሞም የአሉታ አንቀጽ ሆኖ አንድ ነገር ትክክል አለመሆኑን መናገር ማረጋገጥ ነው። 1

ሕያሴ ከውቂያና ከማበራየት ጋር፥ ከውስጥ ፍተሻም ጋር የሚመሳሰል ጠባይ አለው። አሁን የምኖረው የገበሬዎችም አካባቢ ነው፤ ዘመናዊው ሃርቨስተር በአንዴ እየሄደ አጭዶ ወቅቶ ገለባውን ወደ ውጪ እየላከ እህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል። በአገር ቤቱ ግን ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ የውቂያ ጊዜ ይሆናል። ልጅነቴ ከግብርና ጋርም የተቆራኘ ነውና ትዝታውም ያስደስተኛል። በብዛት የምናመርተው በቆሎና ጤፍ ነው። ሰብሉ እንደ ብዛቱና ዓይነቱ በእጅ፥ በዱላ፥ ወይም በአሂዶ ይበራያል፤ ይወቃል። በቆሎን በዱላ ነው የምንወቃው። ጤፍ በአሂዶ ነው። አሂዶ በአውድማ ላይ እህል ተበትኖ ከብቶች እንዲያሄዱት፥ እንዲሄዱበት ማድረግ ነው። ምርቱ ከገለባ የሚለይበት መንገድ ነው።

አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደተረጎሙት፥ ማሸት፥ ማፍተልተል፥ ማበራየት፥ መርገጥ፥ ማልፋት፥ ማፍረጥረጥ ማለት ነው። ስብከት፥ ትምህርት፥ መዝሙር፥ መጽሐፍ ወዘተ፥ ለስሚና ለእይታ ከመቅረባቸው በፊት ሳንሱር ወይም ከቀረቡ በኋላ ሒስ ሲደረግባቸው ገለባውን ከፍሬው የመለየት ሥራ ነው።

ከአምና ጀምሮ እየሠራሁ ያለሁት ሥራ (ከመጋቢነት አገልግሎቴ ጎን የድንኳን ሰፊነት ሥራዬ ማለት ነው) ደግሞ የነዳጅና ጋዝ ዕቃዎችን መፈተሽ (ኢንስፔክት ማድረግ) ነው። የምኖርበት ግዛት የጋዝና ነዳጅ አገርም ነው። በመንግሥት ሕግ ደግሞ እያንዳንዱ ጋዝ የሚታመቅበትና ታምቆ የሚያልፍበት ዕቃ (compressor vessel) እንደ ዓይነቱና መጠኑ በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ መፈተሽ አለበት። ዕቃዎቹ የሚፈተሹባቸው ብዙና የተለያዩ መንገዶች አሉ። እኛ የምናደርጋቸው ሦስት አሉ፤ ከሦስቱ ዋናው ግን UT (Ultrasonic Testing) Inspection የሚባለው ነው።

UT እንደ አልትራ ሳውንድ ቴስት ያለ ነው። እርጉዞች በማኅጸናቸው ያለ ሕፃን እንደሚታየው ያለ ወይም ይህን የመሰለ መሣሪያ ነው። ዕቃው ከውጪ ምንም ችግር የሌለው ሊመስል ይችላል። በውስጡ ግን ብረት መብላት የሚችል አሲድ ያለበት የነዳጅ ድፍድፍ ወይም ኦክሲጅን ያለበት ጋዝ እና ውኃም ስለሚያልፍበት ከውጪ ሳይታይ ከውስጡ

1 መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሓዲስ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤

ዓመተ ምሕረት፤ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ 443 እና 465-466።

Page 3: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

3

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ሊዝግና ሊበላ ይችላል። የተለያዩ መከላከያ ዘዴዎች ቢኖሩም መበላቱ አይቀርም። ስለዚህ ዓመታዊ ፍተሻ ግዴታ ነው።

መሣሪያችን ከውጪ ስንመረምርበት የውስጡን ምስል ወይም ውፍረቱንና ስስነቱን ነው የሚለካና የሚነግረን። ከውስጥ ብዙ ከተበላ የታመቀው ነዳጅ የሆነ ጋዝ ሊፈነዳና ከንብረት ይልቅ በአካልና በሕይወት ላይ ክፉ አደጋ ሊያደርስ ይችላል። ፍተሻው አደጋን የመከላከል እርምጃ ነው።

የሕያሴ ሥራ ከእነዚህ ሁለት ነገሮች፥ ከማሄድና ከውስጣዊ ፍተሻ ጋር የሚመሳሰል ጠባይ ስላለው ነው እዚህ የጠቀስኳቸው። ማሔስ ምርትን ከግርድ፥ ፍሬን ከገለባ መለየት ነው። ውስጡ ባይታይም ውስጡ ምን እንደሚመስል ውስጡን ከውጪ መመርመርም ነው። ውስጡን ከውጪ መመርመር ያልኩት እኛ ውስጥን ማየት ስለማንችል ነው። ልብንና ኩላሊትን መመርመር ስለማንችል ነው። ግልጽ እስካላደረጉት ድረስ መነሣሻ ግፊታቸውን (motive) ማወቅ አንችልም። የሚያስተምሩትን ትምህርት ግን መመርመር እንችላለን። ሙሉው መመርመሪያ በእጃችን ስላለ። ልምምዶቻቸውንም መጠየቅ እንችላለን። የቀደሙት ቅዱሳን ያደረጉትና የሄዱበት ፈር በግልጽ ስለሚታይ። እህል ከገለባ ጋር አብሮ ነው የሚመጣው ብለን ፍሬውን ጠርጥረን መብላት ስንችል ከነገለባው መብላት የለብንም። 'የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ወንዝ ሁሌም የደፈረሰ ነው' ሲሉ ሰምተን ድፍርሱን መግጋት የለብንም። እስኪጠልል መጠበቅ ካልቻልን የምንጠጣውን ወስደን እናጥልለው።

ልጅ ሳለሁ . . . ከላይ የጠቀስኩት መጽሐፍ እንደታተመ በአንድ የምናዘወትረው ምግብ ቤት ለምሳ ተቀምጠን ሳለን አንድ አገልጋይ ወዳለንበት ጠረጴዛ መጥቶ አብሮን ተቀመጠ። ወዲያው ስለ መጽሐፉ ወቀሳ ሰነዘረና በምሬት መናገር ጀመረ። ካሳተመችው ቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንዱ አብረውን ስለነበሩ ያነጣጠረው እዚያ ነው። እኒህ መሪ የሆኑት ሰው፥ "ለመሆኑ መጽሐፉን አነበብከው?" አሉት። "አአይ አላነበብኩትም፤ ሰማሁት እንጂ ርእሱን ነው ያየሁት" አለ። እንዲያነብብ አበረታትተውት፥ "እንደ አገልጋይ መጽሐፍን ሳታነብብ አትተች፤ አንብበው። በል የጻፈውም ይህ ነውና ተዋወቀው" አሉት። ምንተ እፍረቱን ተዋወቅን። ከዚያ ቀዘቀዘ፤ በጣም።

ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ዓመታት ብዙ ስጠየቅ ራሴን እፈትሽም ገባሁ። ልጅ ሳለሁ ስሕተት ፈላጊና ከሳሽ አልነበርኩም። 3ኛና 4ኛ ክፍል ሳለሁ የክፍል አስተማሪያችን የክፍል ሥራ ሰጥቶን ወደ ቢሮ ወይም ወደ ሌላ ክፍል ሄዶ እስኪመጣ ተማሪዎች እንዳይረብሹ የክፍል አለቃ (ሞኒተር ይባላል) ይወክላል። በየተራ ይደርሰናል። አንዳንዱ አለቃ በውኃ ቀጠነ የረባሽ ተማሪዎችን ስም ይጽፍና አስተማሪው ሲመጣ ይሰጣል፤ ረባሾቹ ይቀጣሉ፤ በልምጭ ግርፋት። የኔ ተራ ሲደርስ እንዳይረብሹ እነግራለሁ፤ ትንንሽ ረብሻ የሚረብሹ ጥቂት ይኖራሉ። ግን የማንንም ስም ሳልጽፍ

ቲቸር ከሄደበት ይመለሳል። ስም አለመጻፌ ፍርሃት አይደለም። ግን ለትንንሽ ልጆች በትናንሽ ስሕተቶች ምክንያት መጠማመድ ትክክል አልመሰለኝም። ኋላ ደግሞ ቂሙ መልሶ በኛው ላይ ይበረታል። ሌላ ጊዜ የተገረፈው በተራው አለቃ ሲሆን ያስገረፈውን ተማሪ ስም ባይረብሽም እንደረበሸ ጽፎ ያስገርፋል። አልረበሽኩም ብሎ ተመስክሮለት ሲረታ የጻፈው ደግሞ ይቀጣል፤ ወይም ከምስክሮቹ ጋር ይጣላል።

ሐያሲነትን ወይም ተቺነትን ከወላጆቼም አልወረስኩም፤ አልተማርኩትምም። እናቴ በቃላት መጫወት ትችላለች፤ ነገር ታውቃለች እንጂ ነገረኝነትን አላየሁባትም ነበር። አባቴ ከዋና ተግባሩ ጎን የትርፍ ጊዜ ፈቃደኛ ጠበቃ / ነገረ ፈጅ ነበረ፤ ለሌሎች ነገር እንጂ ለራሱ ግን አይደለም። የራሱን ቦታ ለመልቀቅ ሁሌም ፈቃደኛ ነው። በዚህ እንዲያውም እርሱን እመስላለሁ። አንዴ ከእርሻ ቦታዎቹ በአንዱ የድንበር ግጭት ሆነና ወሰን መካለል ነበረባቸው። በቀጠሮው ቀን ትንሽ ብሆንም (10 ዓመቴ) እኔንም ይዞኝ ሄደ። ሲካለሉ አይ ነበር። የድንበርተኛው መሬት ባለቤት ድንበሩን በከዘራው ይወጋል፤ አባቴም ከራሱ መሬት አንድ እርምጃ ያህል ወደ ውስጥ ገብቶ ችካሉን ያስተክላል። እንዲህ በመሬቱ ርዝመት (500 ሜትር ያህል) 1 ሜትር ያህል ወደ ውስጥ እየገባ ቋሚው ድንበር ተከለለ። በነገረኛ ሰው በየዓመቱ ከመነዝነዝ 500 ካሬ ሜትር መስጠት ቀላል ነው። በዓመቱ 'የመሬት ለአራሹ' አዋጅ ታውጆ ያ ሰው ወደዚያ ሳይመለስ ቀረ። ልጅነቴን ሳስብ አሁን ለምሠራቸውና ለምጽፋቸው የሕያሴ ሥራዎች መሠረት እንደነበረበት የሚያሳየኝ ነገር አላይም። እንዳልወረስኩት አውቃለሁ።

ግን ምናልባት ሒስ ሊወረስም ይችል ይሆናል፤ አላውቅም። ትልቋ ልጃችን ኤላ (ትልቋ ናት እንጂ ገና ትልቅ አይደለችም) ያለ ቦታቸው የሆኑ ጥቃቅን ነገሮችን በቀላሉ የምታይ፥ የምትለቅምና የምታስተካክል ናት። በየጊዜው የእድገታቸው መልክ ይቀያየራልና አሁን ብዙም እንዲያ አይደለችም። ግን እስኪገርመን ድረስ ከመስመር የወጣ ነገር እስኪስተካከል እረፍት የማይሰማት፥ ስፍራ የለቀቀ ነገርን መልሳ ማስተካከል እስክትችል የሚያሳምማት ናት። ከአንድ ዓመቷ ጀምሮ የተመዘገበላት ነገሯ ነው። የምግብ ወንበሯ ላይ ታስራ (እንዳትወድቅ) ምግቧን በመብላት ፈንታ ቦታውን የለቀቀ ነገር እወለል ላይ ይሁን ወይም ሌላ ቦታ፥ እንዲስተካከል ገና ባልተፈታ አፏ ትንጫረር ነበር። አሁን ቀጣይ ደረጃ ላይ ስላለች ይሆናል ቀንሳለች፤ እንዲያውም አዝረክራኪ ሆናለች። ያኛውን ለታናሿ 'ያወረሰች' ይመስላል።

ለመታረም ማወቅ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ባለ ሥልጣን የነበሩ ሌ/ ጀነራል ዓቢይ አበበ የጻፉት አውቀን እንታረም የተባለ መጽሐፍ የሚናገረው እውነት አለ።ይህንን መጽሐፍ 10ኛ ክፍል ሳለሁ ይመስለኛል፤ እንዲያው መጽሐፍ ስለምወድ ብቻ በይርጋ ዓለም የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ማንበብ እንደጀመርኩት ትዝ ይለኛል። ያኔ ብዙም አልስብህ ብሎኝ አጋምሼ ተውሁት። አሁን ግን አነበብኩት። መጽሐፉ በውስጡ የዚያን ዘመኑን ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊም ኹነት፥ ችግርን መገንዘብን፥ መፍትሔ መፈለግን፥ አቅጣጫ መተለምን የሚናገር መጽሐፍ ነው። ደራሲው ለንጉሡ ታማኝ ባለሟልና ወዲያውም አማች ሆነው ሳለ ዘመኑን አመላካች ትዝብት እና የእርማት ጠቋሚ ሥራ መጻፋቸው ድንቅ ነው። ከነጀነራል መንግሥቱ ንዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የታተመ መጽሐፍ ነው። እርማትን የጋበዘው ያ እንዳይደገም ወይም ያንን ያስነሳው ችግር እንዲቀረፍ መሆን አለበት ብዬ እገምታለሁ። አሳዛኙ እውነት ግን መጽሐፉ ያመለከተበትን አቅጣጫ ንጉሡንም ጨምሮ የዘመኑ ባለ ሥልጣናት አላስተዋሉትም ማለት ይቻላል። አውቀው አልታረሙም ማለት ነው።

ስለ ሀገሩ ተቆርቋሪ ያልሆነ ሰው ለሕጓ ተገዥ አይሆንም፤ ድንጋጌዋንም የማያከብር አፉ ይዘልፋታል አሳልፎም ለማይገባው ዘላፊ ይሰጣታል፤ . . . የፖለቲካ ተቃዋሚ

Page 4: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

4

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ወገን የሌለው መንግሥት ሥራው አይሠምርለትም፤ ቢሠምርለትም ከመወቀስና ከሕዝብ ማልጎምጎል አይድንም፤ እንዲያውም ወደ መዋለልም፤ ወደ መንገድገድም ያደርሰዋል። . . . ሁለት የፖለቲካ ወገን ክፍሎች ብቻ መኖርና መደርጀት ለአንድ ሀገር እድገትና ስለ ሕዝቡም መልካም አመራር በቂ ይመስለኛል፤ ይህም አዲስ ነገር ሳይሆን ተደርጎ የታዬ ነውና ልዩ ማስረጃ አያሻውም።2

ቦተለክሁኝ አይደል? ቆዩኝ። ስለ ማኅበራዊው ይዞታ፥ ስለ ትምህርት፥ ሥልጣኔ ከተማረው ወዳልተማረው እንዴት መውረድ እንደሚችል፥ ልማት ወደ ገጠር ብቻ ሳይሆን ወደ ዳር አገር መሄድ እንደሚገባው፥ የየግዛት ጸጥታ በየግዛቱ ሕዝብ እንዲጠበቅ፥ መወዘፍ ቀርቶ የሥራ ባህል እንዲዳብር፥ ባለ ሥልጣን ከከርሳምነት ተላቅቆ ተግባራዊ እንዲሆን፥ ስለ ተፈጥሮአዊ መብቶች ጥበቃ፥ ወዘተ በስነ ምግባራዊ ቋንቋ ነው መጽሐፉ የሚያብራራው። በተለይ፥ 'ሁለት የፖለቲካ ወገን ክፍሎች' የተባለው opposition party ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሚባለው ነገር ይመስለኛል። በንጉሣዊና ፊውዳላዊ አገዛዝ ውስጥ ይህ መታሰቡ ያስደንቅ። ተቃዋሚ ከኖረ እርማት፥ ወቀሳና ሒስ በሽ ነው። ይህ ፍሬ የሚያፈራ የአሳብ ተቃውሞ ያኔ እንዲኖር ያልተበረታታውን ያህል ዛሬም እንደዚያው ነው። በአገራችን ባህል ሕያሴ ያልተወደደ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ የተጠላም ነው።

ይህ መጽሐፍ መጀመሪያ በ1955 ዓ. ም. በአሥመራ ታተመ። ደራሲው በጊዜው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሳሉ ማለት ነው። ለሁለተኛ ጊዜ በ1967 ነው የታተመው። ሁለተኛው እትም በ1967 ዓ. ም. መታተሙ ምጸታዊ ይመስለኛል። ደራሲውም ከ60ዎቹ ባለ ሥልጣኖች አንዱ ሆነው በደርግ መንግሥት የተገደሉት በዚያው ዓመት በኅዳር ወር ነውና። አሁን ይህን እየጻፍኩ ሳለሁ በዚያው ዘመን በጅምላ ከተገደሉት አንዱ ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ታስረው ሳለ ከመገደላቸው በፊት ለመርማሪ ኮሚሲዮን የጻፉትን አስገራሚ ማስታወሻ እያነበብኩ ነኝ። መጨረሻው ላይ ሳያልቅ እንደተቀጨ በሚታየው በዚህ የማስታወሻ ጽፍፉ ከጸሐፌ ትእዛዙ የግልና አገራዊ ሕይወት ባሻገር አገሪቱን በሰላማዊ ዲሞክራሲ መንገድ ለማስጓዝ ከላይ ከሕገ መንግሥት መሻሻል እስከ ገበሬውና እስከ መሬት ይዞታ መሻሻል የተደረጉ ሙከራዎች ይገኛሉ።3 እንደዚያ ያሉ ሰዎች እንደ ዘበት በጅምላ ሲወድቁ መቼም ያሳዝናል። ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሌ/ ጀነራል አቢይን ከርሳቸው ቀጥሎ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ሞክረው ነበር። ሳይሆን ቀርቶ፥ ነገሮችም በፍጥነት ተለዋውጠው በወራት ውስጥ ሁለቱም ከሌሎች ጋር አለቁ። የደርግ መንግሥት ትልቅ ስሕተቱ ገዳይነቱ ይመስለኛል። መለዮአቸውን ለውጦ መለዮው ስር ባለው አእምሮ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ሊያደርግ ሲቻለው ፈጃቸው። መካሪና ተሞክሮ አልባ መንግሥትና የኮሚኒዝም መሞከሪያ መደብ ሆነ። ሒስን በሰፊው ያስተማረ ያ መንግሥት ሒስ ከቶም ያልተዋጠለት ነበረ። ሒስ ኮሶ ነው፤ ይመርራል፤ ግን ያሽራል።

የፈለግሁት የሌ/ ጀነራል አቢይ መጽሐፍ መሪ አሳብ የሆነውን፥ እንታረም የሚለውን አሳብ ነው። እንዴት? አውቀን። ርእሱና ይዘቱ አንድ ናቸው። ለመታረም ማወቅ ግድ ነው። ማወቅ ደግሞ አንደኛ፥ ስሕተቱን ራሱን፤ ሁለተኛም የመፍትሔውን መንገድ ነው። መታረም ካለ ስሕተት ነበረ ወይም አለ ማለት ነው። ሰዎች ነንና እንስታለን፤ እንሳሳታለን። ምንም ነገር ከስሕተት ወይም ከመሳሳት ነጻ አያደርገንም። ክርስትናም። አንዳንዶቻችን እንዲያውም ስሕተታችንን 'ክርስትና አስነሥተን' ትክክለኛና ተቀባይ እንዲሆን እንጥራለን። የኛ ክርስትናም ሆነ የስሕተቱ ክርስትናን መቀባት ከስሕተትነት አያነጻውም። ግን ለመታረም ማወቅ አለብን።

በደርግ ዘመነ መንግሥት ሒስ፥ እና ግለ ሒስ የተባለው ቃል እየሰማሁ ነው ያደግሁት። ወደ ፊት የመሄጃው መንገድ አንዳንዴ ወደ ኋላ

2 ሌ/ ጀነራል ዓቢይ አበበ፤ አውቀን እንታረም፤ ቼምበር ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤ 1976፤ ገጽ 15፥23። 3 ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፥ መስከረም 10 ቀን 1967 ዓ. ም. ለመርማሪ ኮሚሲዮን ያቀረቡት ጽሑፍ።

በመመለስ ነውና አሁንም ትንሽ ልቦትልክ። የሚያሳዝነው እውነት ግን የደርግ መንግሥት ሒስን ያሞግስ እንጂ ራሱን ከሒስ በላይ አድርጎ ነበር የሚያየው። ስለዚህ ለማናቸውም የሚወቀስበት ነገር ጆሮ አልነበረውም።ጆሮ የሚደፍን መሣሪያ ግን ነበረው። እንዲህ ባለ ከባቢ ሒስ የይስሙላ እና ውሸት ነው። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ ግብዝነት የሚባለው ነው።ቢሆንም ሒስን እየሰማሁ ነው ያደግሁት። ሒስ የሌላውን ስሕተት ማሳየትና መንቀስ ነው። ግለ ሒስ የራስን ስሕተት በራስ አውቆ መታረም ነው። እንደ ክርስቲያን ሌላ አንድ ማዕዘን ልጨምርበት። ከራስና ከሌላ በላይ ስሕተትን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን አሳይቶ የሚያነጻም እንዳለን መረዳት መባረክ ነው። ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። መዝ. 10፥12። ስሕተትን ማስተዋል እና ከሚያነጻው አምላክ መንጻትን ማግኘት ብፅዕና ነው። ከዚህ በመነሣት ሒስ ለክርስቲያን የድንጋጤ መድረክ መሆን የለበትም። የሚያሳዝነው ነገር ግን የሚያስደነግጥ መሆኑ ነው። የሕያሴ ሥራዎችን ስለምጽፍ ይህን በቅርብ አውቀዋለሁ።

ሕያሴ እንደ ጉበኛ ማማ ማማ የውጪ ቆጥ ነው። ሁለቱም ቃላት (ቆጥም ማማም) በአማካዩ አንባቢ ላይታወቁ ይችላሉ። ቆጥ እማጀት ውስጥ ወይም ከምድጃ በላይ የሚሠራ በአራት ቋሚዎች ላይ እንደ ጣራ የሚደፋበት፥ አንዳንዴ በጢስ የሚደርቁ ነገሮች የሚንጠለጠሉበት፥ ዶሮዎችም ለማደር የሚሰፍሩበት ነገር ነው። ማማ ተመሳሳይ ነገር ሆኖ በሰብል ጊዜ ወፎችን፥ ዝንጀሮዎችን ወይም ሌላ የአዝመራ አጥፊዎችን በወንጭፍ በሚወረወር ድንጋይ ለመከላከል የሚወነጨፍበት ነው። አንዳንዴ ከፀሐይና ካፊያ ለመከላከል እንደነገሩ ጣራም ይደረግበታል። ያለዚያ ገሳ ለብሶ መቀመጥ ነው። ዋናው ግብ የሰብሉን አጥፊዎች አልሞ መምታት ሳይሆን (ሊምመቱም ይችላሉ) ግን ድንጋዩ የደረቀውን ሰብል ሲመታ ድምጹ ወፉን አስደንግጦት ለማባረር ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሚመስለው ቃል ኢሳ. 5፥2 ያለው ግንብ የሚለው ቃል ነው።

የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ነው። የመጨረሻውን ዘመን ደግሞ በማስጠንቀቂያ ዘርፉ ካየነው፥ 'የጌታ ሥራ ይንሰራፋል' ከተባለው ይበልጥ 'የሰይጣን አሠራር ይበዛል' የተባለበት ይበልጣል። ይህ ጸለምተኝነት ሳይሆን እውነት ነው። በገሃድም እየታየ ነው። ማማ ወይም ከላይ በኢሳ. 5፥2 ያየነው ግንብ የጦር ወይም የጥበቃ ቃልም ነው። በላዩ ቆሞ የሚቃኘው ቃኚ ጉበኛ (በ ሳትጠብቅ፤ እዚህኛው ውስጥ ደግሞ ብ ሳትጠብቅ፤ . . . አማርኛችን የፊደላት ክለሳ ያስፈልገዋል ልበል?) ብቻ ጉበኛ ይባላል። ጉበኛ መሆን ትልቅ ኃላፊነት ነው። የንብረት ሳይሆን የሕይወት ጥበቃ ጉዳይ ነው። በሕዝ. 33፥1-9 የጉበኛ ሥራና ጉበኛው ቢሰንፍ ማስጠንቀቂያው ተዘርዝሮ ተጠቅሶአል። በዚያ ክፍል ሕዝቅኤል ጉበኛ ተብሎአል። የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብሎ የሚናገር፥ የሚመጣውን አደጋ አመልካች አስጠንቃቂ ነው። ሕዝቅኤላ ከባቢሎን ምርኮ ቀደም ሲል ጀምሮ እስከ ምርኮው ዘመናት ያገለገለ ነቢይ ነው። በአስቸጋሪ ዘመን ነው ነቢይ የነበረው። በሕዝቅኤል ዘመን ጉበኛ ማለት በሜዳ ከሆኑ፥ እግረኛ ወይም ፈረሰኛ ቃፊር፥ በግንብ ውስጥ ከሆኑ ደግሞ ከርቀት ቃኚና አስጠንቃቂ ነው።

በኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቃ የሚባል ክፍለ ጦር ነበረ። ኮሪያ ዘምቶ የተመለሰ ከ3ሺህ በላይ ወታደሮች የነበሩት 3 ብርጌድ ጦር ነው። ይህ ጦር ግንባር ቀደም ቃኚ ጦርም ነበረ አሉ። ቃኘው የራስ መኮንን የጦር ፈረስ ስም ነውና ስያሜው ግጥምጥም ይመስለኛል። ላይሆንም ይችላል። ኋላ አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተስማምተው አሥመራ ላይ የተከሉትን ጣቢያ ቃኘው ብለው ሰየሙት። ይህኛው ግን ከስሙም ጋር የተመሳሰለ ነው። እዚያ ሆነው የምሥራቅ አፍሪቃንና የቀይ ባሕርን እንቅስቃሴ፥ ያኔ ሳተላይት አልነበረምና በሬድዮ ሞገድ ይቃኙበት የነበረ ጣቢያ ነው። መቃኘት ከማስጠንቀቅ የሚቀድምና ከማስጠንቀቅ ጋር የተቆራኘ ተግባር ነው። በዘመናችን ደግሞ እውቀቱም መጥቆ

Page 5: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

5

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ቴክኖሎጂውም ተራቅቆ እንቅስቃሴዎች እግር በእግር የሚታዩበት ዘመነ ሳተላይት ሆኖአል።

ወደ ማሔስ ስመጣ ይህ ማሔስ ስሕተትን በመግለጥ ማስጠንቀቅ ነው። የስሕተት አስተማሪዎችን በተመለከተ የሰዎች አቀባበል፥ 1) አሜን ማለትን፥ 2) 'እኔ ደህና ለሌላው ምን ገዶኝ' ማለትን፥ 3) መዝለፍና ማሳደድን፥ 4) ቢቻል ለመመለስ፥ ባይቻል ለማስጠንቀቅ መግለጥን ሊሆን ይችላል። አራተኛው ተገቢውና ሁነኛው ምላሽ ነው። የሕያሴ ግብም ይህ ነው። እኔም ሳሔስ የማደርገው ይህንን ነው። የጉበኛ ሥራ ማስጠንቀቅ ነው። እንደ ሕዝቅኤል አዲስ የእግዚአብሔርን ቃል ወስዶ ማስተላለፍ አይደለም። ቃሉ ተጽፎ ተጠናቅቆአል። አዲስ ቃል የለም። አሮጌው ቃል ግን አያረጅምና አሁንም ሁሌም ትኩስ ነው። ማሔስ ከዚህ ከተጻፈው አሮጌ ግን ትኩስ ቃል አንጻር ማስጠንቀቂያውን መደወል ነው።

ማሔስ በሐሰት ከሆነ ማስበርገግ ብቻ ነው። ልጅ ሳለሁ ያነበብኩት የኤዞፕ ተረቶች ውስጥ ቀበሮ ሳይመጣ 'ቀበሮ! ቀበሮ!' እያለ የሚጮኽ እረኛ ነበረ። ቀበሮ ብሎ ሲጮህ መንደርተኛው ሁሉ ግር ብሎ ይወጣል። ውሸቴን ነው ብሎ ይመልሳቸዋል። ማፌዙ ነው። ሌላ ጊዜም እንዲሁ ያደርጋል። አሁንም ይወጣሉ። አሁንም ቀልድ ነው። ሌላ ጊዜ በእውነት ቀበሮ ወጥቶ በጎቹንም ግልገሎቹም ፈጀ፤ እረኛውም በጩኸት አገሩን ቢያቀውጠውም የሚወጣ አልተገኘም። ለምን? በውሸት ሲያስጠነቅቅ ቆየ። አደጋ ሳይመጣ መጣ ማለት ማስበርገግ ነው። የሚመጣውን ነገር ማስገንዘብ ግን አሸባሪነት አይደለም። ማሔስ በሐሰት ካልሆነ ማስበርገግ አይደለም። ለማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ቀድሞ አደጋውን ያላስተዋሉ፥ ኋላም ጉዳቱን የሚሸከሙ ናቸው።

አሜሪካ በጃፓን የተደበደበችበት የእሁድ ዲሴምበር 7 ቀን 1941 ጠዋት የአሜሪካ ታሪክ ትልቅ ጠባሳ ነው። በ2 ሰዓቶች ውስጥ 6 አውሮፕላን ማረፊያዎች፥ 8 የውጊያ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች (aircraft carriers) 183 ተዋጊ አውሮፕላኖች ተደመሰሱ፤ የጦር ሠፈሮች ወደሙ፥ ወደ 2500 አሜሪካውያን ሞቱ፥ 1178 ቆሰሉ። አሜሪካ ወደ 2ኛው የዓለም ጦርነትም ዘው ብላ እንድትገባ ያደረጋት መንደርደሪያም ሆነ። የዘመኑ የአሜሪካ ፕሬዚደንት፥ 'ያለማስጠንቀቂያ የተፈጸመው ይህ ጦርነት ፍጅት ወይም እልቂት ሆኖ ሲታወስ ይኖራል' ቢልም 353 የካሚካዚዎች የተሳተፉበት የጃፓን ወረራ አንዳችም ማስጠንቀቂያ ያልኖረበት አልነበረም። አንዳንድ የጦርነቱ ተንታኞች እንዲያውም የጃፓን እንቅስቃሴ ቀድሞውኑም ይታወቅ ነበረ እንጂ ዱብ ዕዳ አልነበረም ይላሉ። ከወረራው ቀደም ሲል ሁለት ሰላይ አውሮፕላኖች አካባቢውን ለመቃኘት የቀረቤታ እይታ ማድረጋቸው ሌላው ነው። እነዚህ የሰለሉትና የዘገቡት እንቅስቃሴ ወረራውን ድንገተኛ ላያደርገው በቻለም ነበር።

ሦስተኛው የተናቀው ማስጠንቀቂያ ነው። ይህ በሆነ ጠዋት ከወረራው 1 ሰዓት ቀድሞ ከ300 ኪሜ ርቀት ላይ በፓሲፊክ ውቅያኖስ በሚገኝ አንድ የሬዳር ጣቢያ ይሠሩ የነበሩ የቴክኒሻኖች ቡድን ብዙ ነጠብጣብ እንደሚታያቸው ሪፖርት አደረጉ። ብዙ ነጠብጣብ ማለት በርካታ በራሪ ነገሮች ወይም አውሮፕላኖች ማለት ነው። ቀኑ እሁድ ነበርና ዋናዎቹ አዛዦች በጣቢያው ስላልነበሩ ለአንድ ወጣት አዛዥ ነው የነገሩት። ወጣቱ አዛዥም ከካሊፎርኒያ የሚመጡ የራሳቸው አውሮፕላኖች እንደሆኑ በመገመት፥ “አትጨነቁ፥ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም” አላቸው። ከታዩበት እስከደበደቡበት ባለው አንድ ሰዓት መካከል በቂ የውጊያ ዝግጅት ተደርጎ አደጋው ሊቀለበስ እንኳ ባይችል ሊቀነስ ይችል ነበር። ግን “አትጨነቁ” በሚል የቸልታ ትእዛዝ ውድመቱም እልቂቱም ደረሰ። ይህ ይበቃል እንጂ እንዲህ የመሰሉ በርካታ ታሪኮች አሉ። በኤር. 6፥14 እና 8፥11 ሰላም ሳይሆን ሰላም ሰላም ይላሉ እንደተባሉት ሐሰተኛ ነቢያት በጦርነት ውስጥ የሌለ ሰላምን መስበክ ሰዎችን ማዘናጋት ነው። ሰይጣን 'ተባረረ፤ ካገር ተባረረ' እያልን ስንዘምር እርሱም እንደሚዘምር አንርሳ! አልተባረረም፤ እየዘመረ ነው። ሲመስለን ደስ ይለዋል። ተዘናጋና!

የጉበኛ ሥራ ማስጠንቀቅ ነው። ማስጠንቀቁ ግን ተቀባይነት ሊኖረውም ሊያጣም ይችላል። የሁለቱ የውጤት ልዩነት ግን በቀላሉ የሚገመት አይደለም። አለመጠንቀቅ ጉዳት ነው፤ አውቆ አለመጠንቀቅ ግን አለማስጠንቀቅም ስላለበት ጉዳቱ ድርብርብ ነው።

የመጀመሪያ የወንፈል ድርሰቴ ሳንሱር የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በዓመቱ መጨረሻ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር የሚባለው ወቅት አለቀና በቡድን ሆነን አንድ ቴአትር እንድንደርስ ተጠየቅኩ። የደራሲዎቹ ሰብሳቢ ሆኜም ተመረጥኩ። ከዚያ በፊት ልምዱም፥ እስከማውቀው፥ በጣም ትናንሽ ነገሮችና ግጥም መጻፍ እወድ ነበር እንጂ ተሰጥዖውም ስላልነበረኝ ለምን እንድጽፍና ቡድኑን እንድመራ እንደተመረጥኩ አላውቅም። ምናልባት፥ ዋርካ ሲጠፋ እንደሚመለመለው ግራዋ መሆኑ ነው። ቴአትሩ፥ ማሪኝ አብዮቴ ተብሎ ርእስ ተሰጠው። ተዋናዮች ተመረጡ (አስገራሚ ተዋናዮች ነበሩበት)፤ ተለማመድን፤ ተዘጋጀ። በዚያው ርእስ የተሰየመውን የድራማውን መሪና መክፈቻ መዝሙር (ዘፈን) ደራሲም አቀንቃኝም እኔው ነበርኩ። ግጥምና ዜማ ነገር እንኳ ብታንስም ነበረችኝ። ኋላ ቴአትሩ ተፈትሾ አለፈና በየአውራጃው ሄደን እንድናሳይም ሆነ። ከማለፉ በፊት ግን አንድ ቀን፥ "የአውራጃው (የሲዳማ) ወጣቶች አመራርና ካድሬዎች ይመጣሉና ተዘጋጁ" ተብሎ ተላከብን። እንደ ድርሰቱ ኮሚቴ መሪ ለምን እንደሚመጡ ስጠይቅ፥ "ሳንሱር ሊያደርጉ ነው" ተባልኩ። ሳንሱርን መጀመሪያ የሰማኋት ያኔ ነው። ከኛው መካከል አንዱ ወጣት፥ "ርዕዮተ ዓለሙን የሚጻረር ነገር ከኖረበት ተጠያቂ እንደምትሆን እወቅ" ብሎ ሊያስደነግጠኝ ሲሞክር፥ "እሷ የተጻፈች ቀን የመነጨችው ካንተ እንደሆነች እነግራቸዋለሁ" ብዬው ተሳስቀን ነበር። ያን ቀን ከሥራ ሰዓት በኋላ ሳንሱረኞቹ መጥተው ተመልካቾች ሆኑ። በተለይ ለአስተዋዋቂው ጥሩ ልምምድ ሆነለት።

የአመራር አባላቱና ካሬዎቹ እፊት ወንበሮች ላይ ተቀምጠው (አራት ያህል ይመስሉኛል ሌሎች ደግሞ ስምንት ያህል ከጀርባቸው ነበሩ) ማስታወሻቸው ላይ እየከተቡ ከመጀመሪያ እስከ ፍጻሜው አዩት። ከዚያ በኋላ ተዋናዮቹ ሄደው ደራሲዎቹ ብቻ ቀርተን እስከ እኩለ ሌሊት ቴያትሩን በጣጠቁት፤ ዘለዘሉት፤ አንዳንዶቹ በዶለዶመ ቢላዋ። በዓይናቸው ጥሩ የሆነውን ሁሉ አልፈው መስተካከል ያለባቸው ላይ ብቻ አትኩረው ነጥብ በነጥብ እንድናርምና እንድንሠራው ነገሩን። ይህንን ከተቀበልን (አለመቀበል ለምርጫ መቅረብ አይችልም) ሳንሱሩን እንዳለፈና እንደገና ማየት እንደሌለባቸው ነገሩን። ይህ በግሌ በቀረቤታ ያየሁት የመጀመሪያው የሳንሱር ወይም የእርማት ሥራ ነው። እንዴት ወደድኩት!

ስልታቸውን ብቻ ሳይሆን ራሱን ሳንሱር ወይም እርማት የሚሉትን ነገርና የሥራውን ሂደትም ወደድኩት። መታረምንም ወደድኩት። ብዙ ነገር ይታረማል፤ በተለይ ደግሞ ያን የመሰለው የወንፈል ሥራ የምር መታረም አለበት። ሳንሱር (censorship) መቁረጥ ወይም ማስወገድ ማለት ነው። ከመጽሐፍና ከቴአትር ውስጥ አላስፈላጊ ወይም ጎጂ የሆኑትን ነገሮች ማውጣት፥ ወይም በጦር ሠራዊት ቋንቋ ወደ ጠላት እጅ ቢገቡ ጉዳት የሚያመጡ ሰነዶችን ለቅሞ ማጥፋትና መደምሰስ ማለት ነው። ሳንሱር ከሒስ ልዩነቱ ይፋ ከመሆኑ በፊት፥ ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት መፈጸሙ ነው።

አዲስ 'አገልጋይ' ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነፍሴ አምላኳን አወቀች። ስለ ሕያሴ እየጻፍኩ ስለሆነ ታሪኩን ልዝለለው ብቻ። ጌታን ባወቅሁ በግማሽ ዓመት ውስጥ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት አስመራ ሄድኩ። ያኔ አስመራ ኢትዮጵያ ውስጥ

Page 6: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

6

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ነበረች። አዲስ ክርስቲያን ነኝና ከመሄዴ በፊት በነበሩኝ 6 የመጀመሪያ የክርስትናዬ ወራት መጽሐፍ ቅዱሴን አንዴ አንብቤ ጨርሼ ሁለተኛ ዙር እየደገምኩ ግማሽ ደርሼ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከባድም ቀላልም፤ ግን ጣፋጭ መጽሐፍ ነው። ወደድኩት፤ እስካሁንም በጣሙን። እንደ ባሕር ጥልቅ ነው፤ እንደ መልካ በውስጡ የሚራመዱበትም ነው። ያኔ ቦታዎቹን ፈልጎ ማግኘት ያስቸግረኝ እንጂ አንዴ ስላነበብኩት ያልተጻፈ ነገር እንደተጻፈ ሆኖ ሲነገር የሆነ የወለቀ ነገር እንዳለ ይገባኝ ነበር። ያኔም ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች የተጻፈውን ጎምደው ወይም ያልተጻፈ ነገር እንደተጻፈ አድርገው ሲናገሩ እሰማለሁ። የአዲስ አማኝ ይሉኝታና የተፈጥሮ ልስላሴ ግን እንዳልሞግት ይገቱኝ ነበር እንጂ በቃሉ ውስጥ ያልተጻፈ ነገርን እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርገው የሚናገሩ ሃይማኖተኞችን፥ 'እንደዚያ የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም' ወይም፥ 'የቱጋ ነው የተጻፈው?' ማለት ጀምሬ ነበር።

በነዚያ 6 ወራት ጌታን ለመቀበል ውሳኔዬን ባደረግኩባት የ5 ኪሎ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ የሱስ እና በአጥቢያዬ በኅብረት አምባ ቃለ ሕይወት የክትትል ትምህርቶችን እንደ በጋ መኖ እሰበስብ ነበር። አስመራ ደግሞ በአማኑኤል ቃለ ሕይወት ዲያቆን ሆንኩ። ትግርኛ ለመስማት ምንም ያህል ጊዜ አልወሰደብኝም። ጥሩ የቃሉን አስተማሪዎች አገኘሁ። በዩኒቨርሲቲው በጣም ጣፋጭ ክርስቲያናዊ ኅብረት ነበረን። በዚህ የክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት ከበሳል ልጆች ጋር ቃሉን ማጥናት፥ ቃሉን መበርበር ልበለው፥ ሳምንታዊ ተግባራችን ነበር። ይህ ከቃሉ ያፈነገጡ ነገሮችን አይቼ እንዳላየ እንዳላልፍ በእጅጉ መሠረት ጣለልኝ።

በዚህ ጊዜ ሌላ ያገለገሉኝ የመጻሕፍት ክምችት ናቸው። በኅብረት አምባ ቤተ ክርስቲያን መጋቢዬ አብርሃም ዮሴፍ የአሥመራ ሰው ነበርና አስመራ ከነበሩ ቤተ ሰቡ ጋር ተዋውቄ የማዘወትረው ቤቴ ሆነ። በዚያ ቤት ውስጥ ሁለት መደርደሪያ ሙሉ ክርስቲያናዊ መጻሕፍት፥ የሕይወት ታሪኮች፥ ሐተታ መጻሕፍት (commentaries) እና የመጽሐፍ ቅዱስ መዛግብተ ቃላት አሉ። ለካስ Logos የምትባለው በየወደቡ እየሄደች የክርስቲያናዊ የስነ ጽሑፍ አገልግሎት የምታበረክት መርከብ እ. ኤ. አ. ከOct. 22 እስከ Nov. 15, 1973 ለሦስት ሳምንታት በምጽዋ ወደብ ቆይታ ክርስቲያናዊ መጻሕፍት ለአንባብያን አቅርባ ነበር። ከአብዮቱ ፍንዳታ አንድ ዓመት ግድም ቀድሞ ማለት ነው። እነዚህ መጻሕፍት ያኔ ከምጽዋ ከመርከቧ የተገዙና ሌሎችም በሃይማኖት ዮሴፍ የተባለው የመጋቢ አብርሃም ወንድም በግሉ የሰበሰባቸው የመጻሕፍት ክምችቶች ናቸው። በስደት ዘመን ያ ክምችት ማለት እንደ ታላቅ ድግስ ወይም እንደ በረሃ ምንጭ ነው። በኮሚኒዝም ስደትም በመከራ ያለፉ የነ ሐራላን ፖፖቭ፥ ሪቻርድ ውርምራንድ፥ ዋችማን ኒ መጽሐፎችና ምስክርነቶች ደግሞ ልዩ የስንቅ ምግቦች ነበሩ። በጊዜው የመጽሐፎቹ ባለቤት የሆነው በሃይማኖት አሜሪካ አገር ነበረና፥ መጽሐፎቹን ከኔ በቀር የሚያነብባቸው ስላልነበረ የራሴ እስኪመስሉኝ ደርሰው ነበር። እነዚህ በጣሙን ጠቀሙኝ። ከቃሉ ጋር አያያዙኝ። መስመርም አስያዙኝ።

በዩኒቨርሲቲው ኅብረት ውስጥ፥ "ኧረ፥ ገና ጡጦም አልጣልኩም" እያልኳቸውም የቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጠኚ አደረጉኝ። እየፈራሁ ግን ጀመርኩ፤ የጠቀመኝ ትልቅ ነገር ሁለቴ ማጥናቴ ነው፤ አንዴ ጥናቱን ስናዘጋጅ፥ አንዴ ከቡድኔ ጋር ስናጠናው። ማጥኛውን የምናዘጋጀው ጋሽ በቄ ነው የምንለው (መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን) ቤት ነበር። የመጀመሪያውን ማጥኛ ስናዘጋጅ እርሱ ያስተማረን ትምህርትና የትምህርቱ የተሰደረ መሆን አስደነቀኝ። ክርስቲያኖች ቃሉን በሥርዓት በልተው ሲያበሉት ይጥማል። ከዚያ ሳይርቅ በሌላ ጊዜና ቦታ የዕንባቆምን መጽሐፍ በየብልቱ እየመተረ ሲያስተምረን ደግሞ ተደመምኩ። ያኔ ነው ዳራ እና ዐውድ የሚባሉትን ነገሮች (ቃላቱ በአማርኛ ባይሆኑም) ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት።

መጽሐፍ ቅዱስን በሥርዓት ማጥናት ለመድኩና በጣም ጣመኝ። ቃሉ እንደዚሁም የሚጥም ነው፤ በወግ ሲያጠኑት ደግሞ በጣም የሚጥም ነው! ኋላ በኢቫሱ (አገር አቀፉ የወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት) የInductive Bible Study ሥልጠና አገኘሁ፤ ይህ ከምንባብ

ውስጥ ከተለቀሙ እውነቶች በመነሣት ወደ ጠቅላላ ድምዳሜ የመድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ነው። ቃሉን ስናጠና ዐውደ ምንባቡን መርሳት ከመስመር እንደሚያወጣን ተማርኩ። ይህ ስልጠናም ሌላ ቁርኝት ፈጠረልኝ፤ ከቃሉ ጋር። ጸሐፊው ሊጽፍ የፈለገው ዋና እውነት አለና እንዲያው በመላና በመሰለኝና በአንድምታ መናገር ቀረ ማለት ነው። ይህም አጠናን ለዘለቄታው ረዳኝ። ብዙ ሰባኪዎቻችን ይህችን አጠናን ቢለምዷት ኖሮ ከስንት አጉል ትምህርትና ልምምድ በተረፍን ነበር!

በኋላ ላይ ከደብረ ዘይት አዲስ አበባ በሳምንት ሁለት ቀናት እየተመላለስኩ በአይ ኢ ሲ የማታ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት መማር እንደጀመርኩ ከወሰድኳቸው ቀዳሚ ኮርሶች አንዱ የብሉይና የአዲስ ኪዳናት ዳሰሳ ነበር። ከአስተማሪዎቼ አንዱ ሚ/ር ጄሪ ቤድሶል መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት መጠናት እንዳለበት ሲያስተምረን ማንጎና ቢላዋ ይዞ እክፍል መጣ። ማንጎ በብዛት በሚበቅልበት ጋምቤላ አካባቢ ሚስዮናዊ ሆኖ ሲኖር ማንጎ እንዴት ይበሉ እንደነበር ነው ያሳየን። መጀመሪያ እመሃል ይሰነጥቁታል፤ ጠጣሩ ፍሬው እመሃል ስላለ ወደ ጎን ጠጋ ብለው። ከዚያ ያንን ቁራጭ ሙሉ በሙሉ ሳይሆን እስከ ልጣጩ ድረስ ልክ እንደ እስኩዌር ወረቀት በቢላዋው ሹል ጫፍ ይቆርጡና ልጣጩን ወደ ውስጥ ሲጫኑት እንደ አንኳር ሆኖ ይወጣል። ያንን በጥርስ እያነሱ መብላት ነው!

መጽሐፍ ቅዱስም ልክ እንደዚያ አንድ ክፍል በአንድ ጊዜ ለአፍ ሞልቶ እንደሚጎረስ ሲጠና ትርጉም እንደሚሰጥ ምሳሌዎች እየወሰደ አስተማረን። በአይ ኢ ሲ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እማር የነበርኩት ኋላ ወንጌላዊ ሳለሁ ነው። በአዲስ ክርስቲያንነቴ ግን አንዳንድ ጓደኞቼም ያልሆነው እንደሆነ፥ ያልተጻፈው እንደተጻፈ፥ የተጻፈው እንዳልሆነ አድርገው ሲናገሩ የተናገሩትን ትክክል አለመሆን በድፍረት መናገርም ጀመርኩ። ምናልባት ጓደኞቼ ስለሆኑም ጭምር የደፈርኩ ይመስለኛል።

በዓመቱ መንፈሳዊ መነቃቃት ይሁን መናጋት ውሉ ያልለየ ሁኔታ በኅብረቱ ተፈጠረ። መሸርሸርና መረበሽ፥ መሸበርና መሰበር ሆነ፤ መደፍረስና መፍረስ ሆነ። አንዳንዶች ሳይደፈርስ እንደማይጠራ መንፈሳዊ መነቃቃት አድርገው አዩት። ገና በክርስትና ሁለተኛ ዓመቴ ብሆንም አሁን ከመሪዎቹ አንዱም ሆኛለሁ። በሆነው ነገር በርግጌአለሁ፤ ግን መሸሽ አልችልም። እንዲያውም በሁኔታው ወደ ዳር ያፈገፈጉትን በግል መጎብኘትና እንዳይበተኑ ማበረታታት የኔ ኃላፊነት ሆኖ ተሰጠኝ። በየተራ ልጆቹን እያገኘሁ መረጋጋት ያዝን። መረጋጋቱ እኔንም ይጨምራል። በዚህ ውስጥ በሆኑት ነገሮች ካልተናወጠም በውስጡ ካልተዘፈቀም ማቴዎስ ከሚባል አንድ ወንድም ጋር ስለተከሰቱት ሁኔታዎች ስንጫወት የተናገረው ቃል ለሁሌም የቀረልኝ ሆነ። (ፊቱ ሁሌም ኮስተር፥ ቆምጨጭ ያለ ነው፤ ያኔም ፈታ ሳያደርገው) ቃል በቃልም ባይሆን ያለው ይህ ነው፤ "እንዲህ ያለው ነገር በቃሉ ውስጥ የትጋ ነው የተጻፈው? የሚመራን ቃሉ ነው? ወይስ የጌታን ሥራ የሚመስል ግን ከቃሉ ጋር የሚጋጭ ስሜታችን?" ብሎ ጠየቀኝ። 'በቃሉ ውስጥ የትጋ ነው የተጻፈው?' ጥሩ ጥያቄ ነው። ለራሴም መልሴን በጥሩው ጥያቄ ውስጥ ነው ያገኘሁት። በጥያቄ የተጠቀለለ መልስ!

Page 7: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

7

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ማናቸውም ነገሮች፥ ትምህርቶች ይሁኑ ስብከቶች፥ መዝሙሮች ይሁኑ ደንቦች፥ ልምምዶች ይሁኑ ድርጊቶች፥ መጣጥፎችም ይሁኑ መጽሐፎች፥ ከቃሉ ጋር ከተጋጩ ምን ይባላል? ዝም? ወይስ ሌላ የሚባል ነገር አለ? ዝም አይባልም። ይጠየቃል። ይፈትሹታል፤ ያሔሱታል። ጥቂት መጽሐፎችን አሒሼአለሁ። ከዚያ በፊትም ሆነ በዕዝራ ስርጭቶችም ጥቂቱ ላይ ጽፌአለሁ። አሁንም በተከታታይ እስላም እና ክርስትና የተባለውን መጽሐፍ በየገጹ እያየን ነን። (የዚህኛው ከሒስም አለፍ ያለ ምላሽም ጭምር ነው)። እንዲህ ያሉ ክርስቲያናዊ ሕያሴዎች ሲደረጉ ዋናው መጠየቅ ያለበት፥ 'በቃሉ ውስጥ የትጋ ነው የተጻፈው?' የሚለው ነው። አንዳንዴ የ'አተረጓጎም' ልዩነት ወይም የ'መረዳት' ልዩነት በሚል ሰበብ አንዱ አንድ፥ ሌላው ሌላ ሊል የሚሞከርበት ሁኔታ አለ። ጤናማና ከዐውድ ያልወጣ አጠናን ግን የጸሐፊውን አሳብ በመግለጥ የኛን የአንድምታ አተረጓጎም በቀላሉ ሊያስወግድልን ይችላል። ግን ኮስታራ አጥኚ መሆንን ይጠይቃል። ኮስታራ አጥኚ። ኮስታራ አጥኚ ላልሆነ ሐያሲነት አይመችም።

የመጀመሪያዬ የመጽሐፍ ሒስ አንዳንድ ሰዎች ሥራቸውን ሲያሔሱ ያበሳጫቸዋል። ስለ መጽሐፍ ሒስ ትንሽ ልበል። የመጀመሪያዬ የመጽሐፍ ሒስ (መጀመሪያ የጻፍኩት የመጽሐፍ ሒስ) አንድ አስተማሪዬን በጣም ያስቆጣ ሥራ ነበረ። በዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ ያጠናሁት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ (English Language and Literature) ነው። የዓለምና የአፍሪቃ ስነ ጽሑፍ ቅኝት ኮርሶች ስንወስድ ስለ ኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ቅኝትም አንድ ኮርስ ወስደን ነበር። ራሱን የቻለ ሁለት የስነ ጽሑፍ ሒስ (Literary Criticism) ኮርሶችም ወስደናል። እንዲያውም እነዚህ ሁለት ኮርሶች የስነ ጽሑፍ ሕያሴን መሠረት ያስያዙን በመሆናቸው የሒስ ጽሑፋችን በነዚያ የተማርናቸውን መስመር የተከተለ መሆኑ ግድ ነበረ። የኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ቅኝትን 4ኛ ዓመት ላይ ነው የወሰድነው። ኮርሱን ብቻውን ልዩ የሚያደርገው በአማርኛ መሆኑ ነው። አንድ ሌላ የግዕዝ ኮርስ በአማርኛ (ነጥብ የሌለው የaudit ኮርስ) ወስጃለሁ። ወድጄው። ይህኛውን የወሰድኩት የኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ቅኝት ኮርስን ካስተማረኝ አስተማሪም ጋር ነበር።

የኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ቅኝቱ ኮርስ ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ታሪክ ከዳሰሰ በኋላ ሦስት ዘመነኛ መጽሐፎች ላይ ያተኩራል። ሦስቱ መጽሐፎችም ፍቅር እስከ መቃብር፥ ደራሲው፥ እና ሰመመን ናቸው። አስተማሪው (አስተማሪ እዚያ ሌክቸረር ነው የሚባል) እዚያው አስመራ ዩኒቨርሲቲ ጨርሶ እዚያው አስተማሪ የሆነው የሰመመን ደራሲ ነው። ጽሑፉን ስናዘጋጅ ተማሪዎች በነጻነት በማናቸውም የሦስቱ መጽሐፎች ዘርፎች ላይ ሊተነትኑ፥ ሊያትቱ፥ ወይም ሊተቹ መቻላቸው ተነግሮናል። በነፃነት። ነፃነቷ እንኳ ጥሩ ነች፤ ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ Advanced Public Speaking የሚባል ኮርስ ወስደን አስተማሪው በማናቸውም በምንፈልገው ርዕስ ላይ የ20 ደቂቃ ንግግር እንድናደርግ ፕሮጀክት ከነፃነት ጋር ሰጠን። ነፃነቱ በክፍሉ ውስጥ ብቻ መሆኑን አስረግጦ ነግሮናል። የኔ ስም በZ ስለሚጀምር መጨረሻ ነበርኩ። አጋጣሚው ተገኝቶ ነው? ሰላም በሚል ርእስ ስለ ሰላሙ አለቃ ወንጌል ሰበክሁ። ከኔ ጋር 5 ከሆንነው ክርስቲያኖች በቀር ተማሪዎቹ ተናደዱ። አስተማሪውም ወንጌልን አልጠበቀም። ይልቅስ አንድ የካቶሊክ ቄስ ነበር አብሮን የሚማር እና ከእርሱ ነበር ስብከት የተጠበቀው። አጋጣሚዎችን መዋጀት አስፈላጊ ነው። በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ዳሰሳም የኔን ሒስ እንደ ክርስቲያን ሐያሲ ልሠራው ፈልጌ ንጽጽራዊ ሆኖ የሦስቱም ልብ ወለዶች ሃይማኖታዊ ተጋቦት ላይ ያተኮረ አደረግሁት። ጸልዬበትም ነበር።

ዋናው የሒሱ አካሄድ እንዲህ የሚል ነው። የሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ማኅበራዊ ይዞታ የገነነበት ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ወይም ሃይማኖታዊነት የገነነበት ልብ ወለድ ሊባል ይችላል። ከስዕለት ጀምሮ በምንኩስና የሚያልቅ። የበዓሉ ግርማ ደራሲው ደግሞ ለሃይማኖትና

ሃይማኖታዊ እሴቶች ደንታ የሌለው መጽሐፍ ነው። አምልኮአዊ ፍርሃት (superstition) ቢኖርበትም (የሞት ፍርሃት) ሃይማኖት ጉዳዩ አልነበረም። የሲሳይ ንጉሡ ሰመመን ደግሞ (ያኔ ትኩስነቱ ገና ያላለቀ፥ ደግሞም መቸቱ ድኅረ አብዮት እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሆነ መጽሐፍ ነው፤) ሃይማኖትን፥ በተለይም ወንጌላዊ እምነትን የሚያጥላላ ብቻ ሳይሆን ከቶም ስለ እምነቱ ሳያውቅ ጥላሸት ቀብቶ፥ ፖለቲካ አስመስሎ፥ ከምዕራቡ ዓለም ተጭኖ መጥቶ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የተራገፈ ማስመሰሉ ነው። ሁለተኛው አምላክ ብሎ የሰየመው ክርስትናን ወካዩ ገጸ ባህርይ በዱልዱም መጥረቢያ የተገረደፈ ቅርጽ ነው።

ስሕተቱ ስለማያውቀው ነገር አጥላልቶ መጻፉ ነው። አንዳንድ የልብ ወለድ ደራሲዎች ስለሚጽፉት ነገር ለማወቅና የገጸ ባሕርያቱን ኑሮ 'ለመኖር' ወደ ቀየው፥ ወደ ሰዎቹ ልምምድና ወደ ባለታሪኮቹ ከባቢ የሚገቡት ስለዚያ ነገር አሻራቸው ያረፈበት ጭብጥ እንዲኖራቸው ነው። ማን ሰው ነው ሰውን ከማጅራቱ አይቶ መልኩን መናገር የሚችል? ይህን ነበር ያሔስኩት። ይህን ደራሲ ከሌሎቹ ከሁለቱ መጽሐፎች ይልቅ በርሱ መጽሐፍ ላይ የተጻፈው ነበር ያስቆጣውና ያበሳጨው። ስሜቱን እንደተረዳሁት ደግሞ፥ 'ከስሩ ያለ አንድ መናጢ ተማሪ አቀርቅሮ መስማት በተለመደበት ማኅበረ ሰብ እንዴት ደፍሮ ነው መምህሩን የሚወቅስ?' የሚል ነው። በዚህ ዓይነትማ፥ በLiterary Criticism ኮርስ የተቸናቸው የታወቁ የአፍሪቃና የዓለም ደራሲዎች በቁጣ ከመገንፈል አልፈው በብዕራቸው ጨቅጭቀው ይወጉን ነበር ማለት ነው! ግን የምዕራቡንን ዓለም ጸሐፊዎች በቀረቤታ ካስተዋልኩ በኋላ 'አያደርጉም' ማለት ችያለሁ።

በእርግጥ፥ የጻፍኩት ነገር እርሱን እንዳስቆጣው ሁሉ ስለማያውቀው ነገር መጻፉ ማንንም ክርስቲያን አንባቢ እንደሚያስቆጣው የመሰለ ቁጣ እኔንም አስቆጥቶኛል። ሒሱን በጥሞና ከተቀበለ የስነ ጽሑፍ ሰውነቱን ላደንቅ፥ ካልሆነም በሌላ ቀጣይ ሥራው ስለማያውቀው ነገር ከመጻፉ በፊት ስለሚጽፋቸው ጉዳዮች እንዲያውቅ ወደድኩ። ደግሞም፥ ለማስፈራራት ሳይሆን እውነትም ስለጻፈው ከንቱ ነገር አንድ ቀን መልስ ስለሚሰጥ እንዲያውቀው ብዬ ማቴ. 12፥36 ጠቅሼ ነው የደመደምኩት። ቀድሞ እንደገመትኩትም፥ ኋላ እንደተረዳሁትም ከሌላው ሁሉ ይልቅ ይህኛው ነው ያበገነው። ቃሉ ሕያውና የሚሠራ ነውና። ጽሑፉን ከመስጠቴ በፊት ለጥቂት ጓደኞቼ ሳስነብብ እንዳልሰጠው ነግረውኝ ነበር። በዚያ ዓመት ስለምመረቅ እንዳይጥለኝ ፈርተው ነው። የኔ ፍላጎት በዚያ ወረቀት የማልፍበትን ነጥብ ቢከለክለኝም እውነቱን ግን መገንዘብ እንዳለበት ስለተረዳሁ ነው።

የሕያሴ ጽሑፉን ካነበበ በኋላ ሲመልስልኝ ስድብ ቀመስ የሆነ ግማሽ ገጽ ነቀፋውን (የአገሪቱን ርዕዮት መጻረሬን፥ ኋላ ቀርና ባለ ጠባብ አመለካከት መሆኔን፥ ጩኸቴም የጋን ውስጥ ጩኸት መሆኑን ወዘተ፥) ጽፎ ነበር የመለሰልኝ። ጽሑፉን ሊቀበለው ስለማይፈልግም ሌላ ጽሑፍ በሦስት ቀናት ውስጥ እንድሰጠውና ይህ ካልሆነ በዚያ ወረቀት ምንም ነጥብ እንደማላገኝ ጽፎበት ነበር።

ያስደነቀኝ ነገር ያኔ የኔ ሥራ ሳንሱር ሲደረግ እንዳስደሰተኝ ያለ ነገር ሳይሆን ፈጽሞ ተቃራኒ ነገር ነው የገጠመኝ። ምናልባት ያኔ ያ ሳንሱር ያስደሰተኝ ያን ቴያትር በመምራት የጻፈው መናጢ ተማሪ ሆኖ የድርሰቱን አረም ያረሙት ከኛ የገዘፉ ምሑራን መሪዎችና ካድሬዎች

Page 8: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

8

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

መሆናቸው ሲሆን አሁን እዚህ ያስቆጣው ደግሞ በተገላቢጦሽ ተማሪው አስተማሪውን ማሔሱ ነው። ይህ ከሆነ ሒስ ከላይ ወደ ታች ብቻ ነው መፍሰስ ያለበት ማለት ነው። ከሆነ ደግሞ ሥራው ኅሊናዊ እንጂ ነባራዊ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ከሆነ ትኩረቱ ሥራው ሳይሆን ሰውየው ይሆንና ፍርዱም ሚዛናዊ ሳይሆን ስሜታዊ ይሆናል። ከወሰድኩት የLiterary Criticism ትምህርት ጋር ደግሞ ከቶም የሚጋጭ ሆነብኝ።

የጻፍኩትን ወረቀት (የዚያ ዓይነቱ ጽሑፍ paper ነው የሚባለው በዚያ ቋንቋ) በትክክል መረዳቱ አስደስቶኝ በጠየቀኝ መሠረት ሌላ ጽሑፍ በሌላ ርዕስ በሦስት ቀናት ውስጥ አዘጋጅቼ ሰጠሁት። የመጀመሪያውን የሒሳዊ ግምገማ ጽሑፍ የሰጠሁት ግን በእልህ ሳይሆን ስለማያውቀው ነገር እንዳይጽፍ ወይም ስለሚጽፈው ነገር እንዲያውቅ የተገባ ስለሆነ ነበር። ዩኒቨርሲቲን በሚያህል የትምህርት ተቋምና መድረክ ላይ ሒስ መጠላት አልነበረበትም። ግን የተጠላበት አጋጣሚም ኖረ። የሒስ ጥላቻ እዚያ ከኖረ የትም ሊኖር ቢችል አያስገርምም። የትም!

የፍተሻ ኬላ ሒስ ፍተሻ ነው። ሕያሴ እንደ ፍተሻ ኬላ ወይም እንደ ኬላ ፍተሻ ይመስላል። በፍተሻ ኬላዎች ብዙዎቻችን አልፈን እናውቃለን። አገር ጥለው የሚሰደዱ ሰዎች መንገድ ትተው በጫካና በረሃ አሳብረው ድንበር ያቋርጣሉ።

ደርግ 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች በሙሉ በሰፈራ ጣቢያ ሥራ ስም ወደ ጋምቤላና መተከል ተወስደን ነበር። እኛ በነበርንበት ታታ ዙሪያ በሚባለው የጋምቤላ አንድ ሰፈራ ጣቢያ ከከምባታ የመጡ ሰፋሪዎች ነበሩ። ከመካከላቸው በርካታ ክርስቲያኖችም ነበሩና እኔና በየነ የሚባል የአሥመራ ልጅ እነዚህን እንድናገለግል ሆነ። በድንገት ታፍሰውና በአጭር ማስጠንቀቂያ ተግዘው የመጡ የአገር ውስጥ ስደተኞች ናቸውና ምንም ይህ የሚባል ነገር አልነበራቸውም። ቆልተው የሚበሉት ጥሬ እንጂ የሚፈጩበት ወፍጮ እንኳ አልነበራቸውም። ከተማሪዎች የምናሰባስበውን ክብሪት፥ ሳሙና፥ ትርፍ ልብስ፥ ሌላም እየወሰድን እኔና በየነ እናደርስ ነበር። በኛ ሰፈርና በነሱ መካከል የወታደሮች ኬላ አለ። ያንን ጥሶ ማለፍ ግድ ነው። አንዳንድ ማታ በጨለማና በጫካ ሸቀጣችንን ይዘን እናልፍና አድርሰን፥ ዘምረን፥ መጽሐፍ ቅዱስ አንብበንና ጸልየን እንመለስ ነበር። ኬላው የፍተሻ ቢሆንም ፍተሻው ክብሪትና ሳሙና አይደለም። ብንያዝ ቅጣታችን ቀላል አይሆንም ነበር። አንዴ፥ (ይህኛው ተአምር ነው የሚመስለኝ) ከሰፈር ስንወጣ ደማቅ ጨረቃ ነበረ፤ እኬላው ስንደር ደግሞ ጥቅጥቅ ያለ ደመናና ጨለማ ነበረና በጨለማ ኬላውን አለፍን። ኬላ መፈተሻ ነው። የሚፈተሽ ነገር፥ ማለፍ የሌለበት ነገር አለ ማለት ነው። ኬላና ሒስ ስለሚመሳሰሉ ነው ስለ ኬላዎች የማወራው።

ተወልጄ ካደግሁበት ከሲዳሞ (የያኔው የክፍለ አገሩ ስም እንዲያ ነው) ወደ አዲስ አበባ ስመላለስ ልክ ሲዳሞን ስንጨርስ የምናልፈው አንድ የፍተሻ ኬላ አለ። ጥቁር ውኃ ይባላል። ተሳፋሪ መንገደኞች ሁሉ ከመኪና ይወርዱና መኪናው ይፈተሻል። የሚፈተሸው አንድ ነገር ነው፤ ቡና። ደግሞም ፍተሻው ቀላል አልነበረም። አንዴ አንድ በጣም ወፍራም ሰው ጋቢው መሬት ላይ ተጥሎ በወታደር ዓይነ ቁራኛ እየተጠበቀ ቆሟል። አትኩሬ ሳየው ሰውየው ቦርጫም ሳይሆን የለበሰው ትልቅ ድርብ ሸሚዝ በቡና የተጠቀጠቀ ነው። ከዚያ በኋላ ይመስለኛል መኪና ብቻ ሳይሆን ሰውም እየተፈተሸ ይገባ የጀመረው። አንዴ ከጅጅጋ ስመለስ ደግሞ ደከር ላይ (ሐረር መግቢያ) ጠንካራ ፍተሻ ነበረ። ይህኛው ደግሞ የሰልባጅ ልብስና የኮንትሮባንድ ሸቀጥ ፍተሻ ኬላ ነው። ሁለቱምጋ የሚተኮረው አንድ ነገር ላይ ነው።

አሁን ከምኖርበት ከካናዳ ወደ አሜሪካ በየዓመቱ በበጋ ወራት ቤተ ሰብ ለመጎብኘት እየነዳን እንሄዳለን። ወደ አሜሪካ ስንገባ ኬላው ላይ ፓስፖርታችን ከታየ በኋላ፥ 'ፍራፍሬ ይዛችኋል?' ነው የምንባለው። ወደ

ካናዳ ስንመለስ ደግሞ፥ 'ትምባሆ፥ የአልኮል መጠጥ እና የጦር መሣሪያ ይዛችኋል?' ነው የምንጠየቀው። ኬላ መፈተሻ ጣቢያ ነው። ብዙ ነገር ሊጠበቅ ይችላል፤ ግን ዋና የሚፈተሽ ነገር አለ። ትኩረት የሚደረገው እዚያ ነገር ላይ ነው።

አገልጋዮች ወደ መድረክ ሲወጡ 'የሕዝብ ንብረት' ይሆናሉ። በረከትነታቸውም ጉዳታቸውም አድማሱ ይሰፋል። እና ጠንቃቃ ሊሆኑ የተገባ ነው። እንዲያውም ጠንቃቃ ሊሆኑ ግድ ነው። እነዚህ አገልጋዮች በየኬላው ሊያልፉና ሲያልፉም ለመፈተሽ ፈቃደኛ ካልሆኑ የሚጎተቱ ዝተቶች ይበዛሉ። አገልጋዮች ከስሕተት በላይ አይደሉምና ለሒስ የተዘጋጁ መሆናቸው ተገቢ ነገር ነው። ይህ ሐያሲዎቹን ከስሕተት በላይ አያደርጋቸውም። ከቶም። ፈጽሞም። ስሕተት ግን አለመታየት ሳይሆን መታየትና ታይቶም መታረም ያለበት ነገር መሆኑን ማወቅ አለብን። ፍተሻ መፈራት የለበትም። ላለመፈተሽ ብለን በጥሻ ውስጥ መሄድ የለብንም። ከላይ ያልኩት የጥቁር ውኃ ፍተሻ ላይ በእግር ማለፍ አይቻልም። ወንዙ ረግረጋማ ነው፤ ያለው አንድ ድልድይ ብቻ ነው። ግን ከይርጋ ዓለም ስንወጣ አቦስቶ የሚባል ሌላ የፍተሻ ኬላ አለ። የቡና ነጋዴዎች ከሾፌሮች ጋር ተመሳጥረው ያንን ኬላ ሳይደርሱ ከወዲህ ይወርዱና ቡናውን ተሸክመው በጥሻና በሰው ጓሮ እያደረጉ ኬላውን አልፈው እንደገና ይሳፈራሉ።

አገልጋዮች ፍተሻን መፍራት የለባቸውም። በእውነት። መጽሐፍ ሳይታተም ቢፈተሽ ወግ ነው። ከታተመ በኋላ ቢፈተሽም ማስደንገጥ የለበትም። ሰባኪዎችና አስተማሪዎች አስፈትሸው አይሰብኩም። ራሳቸው ሲዘጋጁ እንዲፈትሹ ግን ይጠበቅባቸዋል። የተደመጠ ስብከታቸው ቢፈተሽ ይህም ማስደንገጥ የለበትም። በአጠቃላይ ፍተሻ መፈራት የለበትም። ኬላ ላይ መኪና ሲቆም የሚፈራ ማለፍ የሌለበትን 'ሸቀጥ' የያዘ ብቻ ነው። ማንም ሰባኪና አስተማሪ ራሱን ከጥያቄ በላይ አድርጎ ማየት የለበትም። ተፈትሾ እንከን የማይገኝበት ቅዱስ ቃሉ ብቻ ነው። የሚገርመው እርሱም ተበጥሮ ተፈትሾአል።

መጽሐፍ ቅዱስም ሲፈተሽ በአንድ የእሁድ ትምህርት ቤት አስተማሪዋ የ4 እና 5 ዓመት ተማሪዎቿን፥ "ልጆች መጽሐፍ ቅዱሳችሁ ውስጥ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ?" ብላ ጀመረች። ስለ አስደናቂዎቹ ታሪኮች ልትነግራቸው ነው። አንዲት ትንሽ ልጅ፥ "አዎን፥ የአባዬ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን እንዳለ አውቃለሁ" አለች። አስተማሪዋም ተሳታፊ ስላገኘች ደስ ብሏት፥ "ጎበዝ! ንገሪን" አለቻት። እሷም፥ "አባዬ ሰዓት የገዛበት ደረሰኝና ለእናቴ የጻፈላት ካርድና አክስቴ ከየት ነበር? የላከችልን ካርድና የትንሹ ወንድሜ የልደት ካርድ" አለቻት። "እሱን ማወቅሽ በጣም ያስገርማል!" ብላ ማንበብ ስትችል እውስጡ የተሸጎሩትን ሌላ ነገሮች ሳይሆን ታሪኮቹንም እንድታነብብ አበረታትታ ማስተማሯን ቀጠለች።

ወደ ሴሚነሪ ክከሄድኩ በኋላ ከወሰድኳቸው ትምህርቶች አንዱ Biblical Criticism ነው። ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ሕያሴ ማለት ሳይሆን ራሱ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚፈተሽበት፥ 'ወላልቆ' የሚታይበት ኮርስ ነው። Textual Criticism, Source Criticism, Redaction Criticism, Form Criticism ወዘተ፥ የሚባሉ ወደ 10 ያህል የተለያዩ ሕያሴ ዓይነቶች እንደ ናዳ እየወረዱበት ይፈተሻል። ቃሉን ሰምቼዋለሁ። አስመራ ሳለሁ ካነበብኳቸው የስነ መለኮት መጻሕፍት መካከል በአንዱ እና ደብረ ዘይት ሳለሁ አዲስ አበባ እየተመላለስኩ የማታ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስማርም ስለ Biblical Criticism አንብቤአለሁ፤ ጥልቅ ባይሆንም።

ፍተሻ ለቤትና ለመኪናና ለሰው ብቻ ነበር የሚመስለኝ። በደርግ ዘመን መጨረሻ ነበር ለስነ መለኮት ትምህርት የወጣሁትና ፍተሻ ከሰውነቴ ጋር ተዋህዶ ስለነበረ ወደ ትልቅ ሕንጻ ስደርስ ጠመንጃ ዘቅዝቆ የያዘ ሰው እፈልግ ነበር። አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ፤ ጓደኞቼ አልበርታ የሚባለው

Page 9: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

9

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

አሁን የምኖርበት ጠቅላይ ግዛት የፓርላማ ቤቱን እንዳይ ወሰዱኝ። እኔ ፎቶ ማንሣት እንደሚቻል አስረግጬ ጠይቄ እያነሣሁ ሳለሁ ጓደኞቼ ቀድመውኝ ዘልቀው ነበር። አስረግጬ የጠየቅሁትም የኛ የአራት ኪሎ ፓርላማና ቤተ መንግሥት ሰፈር ፎቶ ስለሚከለከል ነው። እዚህኛው ዘንድ ግቢም የለም፥ በርም የለም፥ ወታደርም አጣሁ። ግን በር የመሰለኝ አካባቢ ቆሜ መታወቂያ ከጠየቁኝ ለማሳየትም ተዘጋጅቼ ፈታሽ እጠብቅ ነበር። ፈታሽ አለመኖሩ በእውነት አስደንቆኛል። በዚያው ዓመት በጋ ላይ እኖርበት ከነበረው ከቫንኩቨር እስከ ቶሮንቶ ከ4ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በአውቶቡስ አገር እያየሁ ተጓዝኩ። አንድም የፍተሻ ኬላ አላየሁምና በዚህም ተገረምኩ። ቆይቶ ነው ልዩነታችን የገባኝ። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ፍተሻ ልመለስ።

በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ፥ በቅዱሱ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ያለ ኮርስ መታሰቡ 'ልክ አይደለም' አሰኘኝ። መጽሐፉ አሳዘነኝ። ኋላ ግን ፍተሻው ወንጀሉን ሳይሆን ወንጌሉን መግለጡን ስረዳው ወደድኩት። ንጹሕ ሰው ኬላ አይፈራማ! ሌሎች ሃይማኖቶች በመጽሐፋቸው ላይ ይህ እንዲደረግ አይፈቅዱም። ሌሎቹ መጻሕፍት እንዲህ ሽንፍላቸው ተገልብጦ ቢፈተሽ የሚገኝበትን ዝባዝንኬ ያውቁታላ! መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለተቺዎች ፍተሻ፥

መገፋት 'ማይፈራ . . . ቅቤ 'ንደሚወጣው እንደ'ርጎ የረጋ፤ መታየት 'ማይፈራ . . . ቀትር እንደሚሆን እንደ ጥዋት የነጋ፤ መፈተሽ 'ማይፈራ . . . እግሩን አንፈራጥጦ እጁን የዘረጋ፤

መጽሐፍ ነው። ከአንድ ስለ መጽሐፉ ከከተብኩት ግጥሜ መሐል የመዘዝኩት ሐረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እግሩን አንፈራጥጦ እጁን የዘረጋ ፍተሻ የማያስፈራው መጽሐፍ ነው። ምንጩን ስለምናውቀው በአክብሮት ከመሆኑ በቀር ለነገሩ ስናጠናውም እንጠይቅ የለ? እንበረብር የለ? በመጽሐፍ ቅዱስ ይህ ከተደረገ የጠራና የነጠረ የመሆኑ ፍተሻ ነው። በሌሎችም መጻሕፍትና ሥራዎች ላይ ጥያቄ ቢነሣ ለምን አስገራሚና አስደንጋጭ ይሆናል? ሰዎች የጻፏቸው መጻሕፍትና የሰበኳቸው ስብከቶች፥ ያስተማሯቸው ትምህርቶችና የዘመሯቸው መዝሙሮች ቢበረበሩ፥ ቢሰበጠሩ፥ ለምን ኡ! ኡ! ይባላል? ለምን?

የስነ መለኮት ትምህርትን ለማጥላላት በስብከቶቹ ደጋግሞ፥ 'ቲዮሎጂ ማለት የተቆላ እህል ነው' የሚል አንድ ወንድም ነበረ። በኋላ ጥሬው ሆዱን አሳመመው መሰለኝ መቆርጠም ጀመረ። ስነ መለኮትን እያጥላሉ ስነ መለኮታዊ ይዘት ያለው ትምህርት ማስተማር አይቻልማ! መጽሐፍ ቅዱስን እያጥላሉ ቃሉን እንደመስበክ ያህል ነው። ስነ መለኮትን የሚያጥላሉ ሰዎችን ስብከትና ትምህርት በቀላሉ መለየት ይቻላል። ቃሉ ላይ ሳይሆን ልምምድ ላይ ያተኩራሉ። ልምምዱ ደግሞ በየጊዜውና ቶሎ ቶሎ ስለሚያረጅና ስለሚሰለች አዳዲስ ልዋጭ ከስር ከስር መፈጠር አለበት። መቀፍቀፍ አለበት። መገንደስ ሲያረጅ፥ መሳቅ ተጀመረ፤ መሳቅ ሲያረጅ ማጓራት ተጀመረ፤ ማጓራት ሲያረጅ ማማጥ ተጀመረ፤ አሁን እየተማጠ ነው ሌላ ለመውለድ። ልምምዶቹ ፍጻሜ የላቸውም። ለሥጋዊ ክርስቲያን ጆሮ የሚጥም ተረታዊ ትምህርታቸውም ማለቂያ የለውም።

ኩረጃው ደግሞ ልክ በካርቦን ኮፒ እንደሚደረግ ያለ ሆኖ ትምህርትን ብቻ የያዘ ሳይሆን አለባበስና እንቅስቃሴንም የጨመረ ነው። ልብሱ እንዲያውም እነዚያ የለበሱት እራሱ የተለገሳቸው ሳይሆን አይቀርም፤ እንደ ኤልያስ መጎናጸፊያ ይሆን? አንድ ሰነፍ ተማሪ አንዱን ስሙንም እንኳ በደንብ የማያውቀውን የክፍሉን ጎበዝ ልጅ ጠርቶ፥ 'ስሚ፥ የዛሬውን ፈተና ካላስኮረጅሽኝ እውጭ እንገናኝ' ብሎ አስፈራራው። ጎበዙ ተማሪም ፈተናውን ቶሎ ጨርሶ ሠራና አስኮረጀው። የመጀመሪያዎቹ ጥያቄዎች አጫጭር መልሶች ነበሩ። ሰነፉ ተማሪ የጎበዙን ተማሪ ስም አያውቅም ነበርና የልጁ ስምም የጥያቄ መልስ መስሎት የልጁን ስምም ጽፎ ለአስተማሪ ሰጠ። ውጤቱን አገኛታ! አንዳንድ ሰባኪዎች ሲኮርጁ ምኑንም ሳያስቀሩ ነው። እና ራሳቸውን መሆን ያቅታቸዋል። ስማቸውንም የለወጡ አሉ። አንድ ወንድም አንዴ መኮረጅንም ስለጨመረ የስሕተት ልምምዶች ትምህርት ከሰጠሁ በኋላ፥ "ሰዎችን መምሰል ምን ክፋት አለበት? ጳውሎስስ እኔን ምሰሉ ብሎ የል?" አለና ጠየቀኝ። አዎን ብሎአል፤ ግን እኔን ምሰሉ ከማለቱ በፊት፥ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል ብሎአል፤ 1ቆሮ. 11፥1። ስለዚህ ጳውሎስን መምሰል ክርስቶስን መምሰል ነው። እውነትም የጳውሎስን ሕይወትና ትምህርቶች ስንመረምር ክርስቶስን ይመስል እንደነበር በገሃድ የሚታይ ነው። የነዚህ መኮረጅ ችግሩ ክርስቶስን ሳይሆን ሰዎቹን ብቻ መምሰላቸው ሆኖ ራሳቸውንም እንዳይሆኑ፥ ክርስቶስንም እንዳይመስሉ ማድረጉ ነው።

የመጀመሪያ መጽሐፌ 'ሒስ' ከቀደም ብዬ የጠቀስኩት የመጀመሪያዬ የመጽሐፍ ሒስ ሲሆን ይህኛው ደግሞ የመጀመሪያው መጽሐፌ 'ሒስ' ነው። ሒስን በትእምርተ ጥቅስ ያደረግሁት ሙሉ ሒስ ሳይሆን እርማት ወይም ሳንሱር ስለሆነ ነው። በወንጌላዊ ክርስትና ውስጥ የመጻሕፍት እጥረት መኖሩ የታወቀ ነው። ይህንን በጥቂቱም ለመቅረፍ ሲባል በቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ስነ ጽሑፍ አገልግሎት (ያኔ ገና የዳበረ የስነ ጽሑፍ አገልግሎት ክፍል አልነበረም) በኩል ወደ 15 ያህል የትመማ (ትምህርተ መለኮት በማስፋፋት - Theological Education by Extension) መጻሕፍት ለማዘጋጀት ሥልጠና ተሰናዳ። እኔም ከጸሐፊዎቹ አንዱ እንድሆን ተጋበዝኩ። የትመማ መጻሕፍት በሳምንት አምስት ቀናት በየቀኑ ለብቻ፥ በሳምንት አንዴ ደግሞ ከአስጠኚ ጋር የሚጠና ለሳምንታትና ለቀናት የተከፋፈሉ ትምህርታዊ መጻሕፍት ናቸው።

ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ በቀጥታ ወደ ወንጌል አገልግሎት ነበር የተሰማራሁትና በደብረ ዘይት ውስጥ በወንጌላዊነት አንድ ዓመት ጨርሼ ሁለተኛው ላይ ነኝ። መጽሐፍ ለመጻፍ ልምዱና ዝግጅቱ ባይኖረኝም አሁን እንደ 11ኛ ክፍል ጊዜው ሳይሆን አሁን የቋንቋና ስነ ጽሑፍ ትምህርቱ አለኝ። ስልጠናውን በሆሳዕና ቃለ ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ውስጥ የሰጡን ከቃለ ሕይወት አቶ ዮሴፍ መና እና ከኤስ አይ ኤም ደግሞ ሚስ ሚና ሞን ናቸው። አሳቡ በ2 ሳምንት እምቅ ስልጠና ተሰጥቶ በ3 ወራት ሥራ 15ቱም ሰዎች 15 የትመማ መጻሕፍት ጽፈው ጨርሰው ወደነበሩበት እንዲመለሱ ነው። ጥቂት የካበተ ልምድ ያላቸው ሰዎችም በመካከላችን ነበሩ። የኔ መጽሐፍ ጭብጥ የወንጌል ስርጭትና ደቀ መዝሙርነት ሆኖ የ8 ሳምንት የጥናትና የተግባር መጽሐፍ ነው። ከአገልግሎት ተለይቼ ሦስት ወራት መቆየት ስለማልችል ስልጠናውን ወስጄና የመጽሐፉን ቢጋር (outline) ከናሙና ምዕራፍ ጋር ሠርቼ ታይቶ ወደ ደብረ ዘይት ተመለስኩ።

ከመመለሴ በፊት ግን የኔ ሥራ በተለይና በጥልቀት መታየት ኖረበት። የኔ በተለይ የታየው በሦስት ምክንያቶች ነው። መታየት ብቻ ሳይሆን እንደገና ፈርሶ ነበር የተሠራው። አንደኛ፥ አዲስ ጸሐፊ ስለሆንኩ። ሁለተኛ፥ የማታ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አዲስ አበባ እየተመላለስኩ እማር ነበረ እንጂ ሁነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጠና ስላልነበረኝ። ከኔ በቀር ሁሉም በአገር ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሩ

Page 10: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

10

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ብቻ ሳይሆኑ አብዛኞቹ የሚያስተምሩ ናቸው። ሦስተኛ፥ ሥራውን እቤቴ ወስጄ ስለምሠራው በየጊዜው እየታየ የማይታረም ስለሆነ (ያኔ በኢንተርኔት እየተቀባበሉ መሥራት አልነበረም)። በነዚህ ምክንያቶች ጅምር ሥራው በጣም ተፈተሸ። እና ቢጋሩ ከጸደቀ በኋላ ናሙናው ምዕራፍ እንደ ፈርስ እየተገለበጠና እየተላጠ ነበር የታረመው። ሁለቱም፥ አቶ ዮሴፍም፥ በተለይም፥ ሚስ ሞን እየፈለፈሉ አረሙት። ሲያርሙት ምንም ምሕረት ባለማድረግ ነበረ። ይህንን የእርምት ሥራ በጣም ወደድኩት።

ይህ ብቻ አልነበረም። ይህንን መጽሐፍ ሳልጨርስ ለስነ መለኮት ትምህርት ወደ ውጪ የምሄድበት ሁኔታ ተፈጠረ። ከመሄዴ በፊት ለመጨረስ መጣደፍ ሆነ። ጨርሼ አስረከብኩ። የታተመው እኔ ውጪ ለትምህርት በነበርኩበት ጊዜ ነበር። ለእረፍት ስመለስ ሳየው የሠራሁት የእጅ ጽሑፍ እንደገና በሁለቱም አሰልጣኞች ታርሞ በጣም መልካም ሥራ ነበር ያደረጉት። አዲስ ሕይወት ማዳረስ በሚል ርእስ ታትሞ ጥሩ የወንጌል ስርጭት እና የአዳዲስ አማኞች መከታተያ ሆኖ አሁንም ይሠራበታል።

ይህ ፍተሻና እርማት ልክ እንደ ወንፈል ድርሰቱ ሳንሱር ማለት ነው። የሳንሱር መልካምነት ሥራው ገና በሂደት ላይ ስለሆነ የተበላሸው በቀላሉ ሊታረም ስለሚችል ነው። የተጨረሰ ሥራ አይታረምም። ከተሳሳተ ይወቀሳል እንጂ ለመታረም ስፍራ የለውም። የተሰራጨ ስብከት፥ የታተመ መጽሐፍ፥ በገበያ ላይ የዋለ መዝሙር፥ ወዘተ፥ አይታረሙም ሒስ ይደረግባቸዋል እንጂ። የሚደረግባቸውም ያን የመሰለ ስሕተት ወደፊት እንደገና እንዳይደገም ነው። ለዚህ ነው ከሥራው በፊት የፍተሻና የእርማት ሂደት፥ ከተሰራጨ በኋላ ደግሞ ሳይታረም አደባባይ በወጣው ላይ ሕያሴ መካሄድ ያለበትና የሚካሄደው።

ለማሳረም ልምዱ የሌላቸው ልምዱን ሊያዳብሩ የተገባ ነው። ለማሳረም ደግሞ ቀድሞውኑ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ይህንን ካልሆኑና ሥራው አደባባይ ከወጣ በኋላ ግን ሕያሴ ቢደረግበትና 'ተጠየቅ' ቢባሉ መደንገጥና ወደ ዛጎላቸው ውስጥ መግባት፥ ወይም አግጥጦ ለመናከስ መውጣት አስፈላጊ አይደለም።

ይድረስ ለዘማሪዎች / የዋህ ስሕተቶች በየዋህነት የተደረገ ስሕተት አውቆ ከተደረገው ስሕተት ልዩነት የለውም። የአድራጊው ግፊት ሊለያይ ይችላል። ግን ስሕተቱ ስሕተት ነው። በጦርነት ወቅት በወገን ላይ አንዳንዴ የወገን መሣሪያ ጉዳት የሚያደርስበት ጊዜ አለ። ይህን friendly fire ይሉታል። አንድ በቅርብ የማውቀው ፓይለት ወንድም ተዋጊ አውሮፕላኑ በወገን ሚሳይል ተመትቶ ሲከሰከስ እርሱ ዘልሎ ሊተርፍ በቅቶ ነበር። ጦሩ የወገን ጦር መሆኑ ወይም ሆን ተብሎ ለመጉዳት ታስቦ የተተኮሰ አለመሆኑ ጉዳቱንም ሆነ ውጤቱን ፈጽሞ ቀላል አያደርገውም።

የስሕተት ትምህርቶችም በስሕተትና በየዋህነት መተላለፋቸው ጉዳቱን አያሳንሰውም። ስለ የዋኅነት ስሕተት ሁላችንም መረዳት አለን። በቅርብ አንድ አስተያየት ስለ መዝሙሮች ተላከልኝ። ከጥቂት ዓመታት በፊት በመዝሙሮች ላይ ስለሠራሁትና ስለበተንኩት ይድረስ ለዘማሪዎች ስለተበኑት ሁለት የኦዲዮ መጣጥፎች ነው። የአስተያየቱ ዋና አሳብ ዘማሪዎቹ እነዚያን ስሕተቶች የዘመሩት አውቀው ወይም ሆን ብለው አለመሆኑ ላይ ያተኮረ ሆኖ ጀማሪዎቹ ዘማሪዎች የሚያርም በመኖሩ ደስ ሲሰኙ አንድ አንጋፋ ዘማሪ ግን በጉዳዩ በጣሙን መቆጣቱን የያዘ ነው። ቁጣውና አትንኩን ባይነቱ በአንጋፋው ላይ መታየቱ ያስገርማል፤ በስሎ ፈር ማስያዝ የነበረበትን የእርሱን ሥራ እኔ ስለሠራሁለትም እንኳ ደስ አላለውም።

እውነት ነው፤ አብዛኞቹ፥ ምናልባት ሁሉም፥ አውቀው አይደለም እነዚያን ስሕተቶች የዘመሩት። ታድያ ሳያውቁ ነው ተብሎ ዝም መባል

አለበት ማለት ነው? የመዝሙሮች እየተበላሹ የመሄድ አዝማሚያ እንደ ጉዳይ በወል ካልተወሳ በመጣጥፎቹ የተነሡትን ዘማሪዎች በነጠላ ለማግኘት የማይሞከር እንዲያውም የማይቻል ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ አትንኩኝ ካሉስ?

መዝሙሮቻችንን በተመለከተ ችግሩ በቀላሉ የሚቀረፍ አይደለም። ዛሬም እጅግ የበዙ መዝሙሮቻችን በቋንቋ፥ በተለይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱሳዊና በስነ መለኮታዊ ሕጸጾች ጢም ብለው የተሞሉ ናቸው። የግል የሕይወት ጥራት፥ ለምን እንደሚዘምሩ የማያውቁ መዝሙረተኞች ብዛት፥ የመታወቅና የዝና ራብተኞች፥ የገንዘብ ሠሪዎች፥ ሌሎችም ጉዳዮች ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉ አሉ። ዛሬም የነቶሎ ቶሎ ቤት ዓይነት መዝሙሮች ከደፍ እስከ ገደፍ ናቸው።

ዛሬም የ'ሲ-ሴክሽን' መዝሙሮች ብዙ ናቸው። ያልተማጠባቸው መዝሙሮች ማለቴ ነው። ላብራራው። ይህ የሲ-ሴክሽን ወሊድ ለመዝሙሮች ብቻ ሳይሆን ስብከቶችና ትምህርቶችም የሚወለዱበት አወላለድ ነው። አንዳንድ እንሰሳት ያለ ጭንቅ ይወልዳሉ። ከጥቂት ወራት በፊት ወደ መስክ ሥራ ስሄድ (እዚህ አገር ላሞች የሚወልዱት በጸደይ ወራት ከኤፕሪል እስከ ጁን ነው) አንዳንድ ላሞች በቁማቸው ዱብ አድርገው ዞረው ሲልሷቸው አይቻለሁ። የምጥ ጭንቅ ለሔዋን እና ለሴት ልጆችዋ ብቻ የተሰጠ ስለሆነ እንሰሳትና አራዊት ይህ የለባቸውም፤ እንደምገምተው። በዚህ ዘመን ግን የሔዋን ልጆችም ምጥ እየቀረ ቀድዶ ማውጣት ተራ ነገር ሆኖአል። ይሁን እንጂ፥ የምጥ ልጆች እና የሲ-ሴክክሽን (Caesarian Section) እናት ሳታምጥ ሆድ ተቀድዶ የሚወለዱ ልጆች ልዩነት አላቸው። በልምድም በሳይንሱም እንደተረጋገጠው በምጥ የሚወለዱ ልጆች በመጨረሻዋ የምጥ ሰዓት ከእናት የሚመነጭ ቅመም እና ሌላም ለአንጀት ጠቃሚ የሆነ ነገር በማኅጸን ጠባብ አፍ ሲወጡ ያገኛሉ። ሆድ ተቀድዶ የሚወጡቱ ያንን ሳያገኙ ነው የሚወጡት። እናም ለተለያዩ አለርጂዎች፥ ለውፍረት፥ ለሌሎችም ነገሮች የተጋለጡ ናቸው ይባላል። የምጥ መዝሙርና የዘጥ ዘጥ መዝሙርም እንደዚሁ የተለያዩ ናቸው። ደግሞም በምጥና በእንብርክክ የተወለዱ መዝሙሮችና 'እየሮጠች ዕንቁላል ጣለች' መዝሙሮች ያስታውቃሉ። እነዚህ ወዲያው ይጠወልጋሉ።

በይድረስ ለዘማሪዎች ሁለት የመዝሙር ሕያሴዎች ስሕተቶቻቸውን ሲያውቁት ለመታረም የቻሉ አሉ። ሊቀረጽ የነበረ የመዝሙር ቀጠሮም ተሰርዞ መዝሙሮች እንደገና ተፈትሸው መታረማቸውን የነገረኝ አገልጋይ አለ። ይህ ስሕተቶቹን ላለመድገም መራመድ ነውና ሸጋ ነው። ግን ይህ በሁሉም ዘንድ የለም። ልክ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዬ እንደወረደብኝ ከዘማሪዎችም ከዚህ ያላነሰ ያደረጉ አሉ። አንድ ሊደበድበኝ የዛተብኝ ዘማሪም አለ። 'በሥጋ እንዳልገለጥብህ እረፍ በሉት' የሚል መልእክት ነበር እንዲደርሰኝ ያደረገው። ይህንስ ምን ይሉታል? ጉድ ነው! ማሔስ አንዳንዶችን በሥጋ እንዲገለጡም ያስደርጋል። በሥጋ መገለጥ የአዲስ ኪዳን ቋንቋ ሆኖ አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ሥጋ ሲለብስ የሆነው ኹነት ነው። ይህ ዘማሪ ሊል የፈለገው ምናልባት 'በቡጢ እዘርርሃለሁ' ነው። ሌላ ነገር ካልተጠቀመ በቀር። ግን ይህንን ቃል (በሥጋ መገለጥ የሚለውን) መጠቀም ቢፈራ መልካም ነበር። ይህ 'ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ' ከሚለው የጌታን ማዕረግ ለምድራዊ ንጉሥ ከመጫን የተለየ አይደለም። ይህ ዘማሪ ልክ በመዝሙሮቹ ቃላት እንደሚያደርገው ሁሉ 'በሥጋ መገለጥ' የሚለውን ቃል እንደ ብይ ሲያንከረባብተው ድንግጥም አላለም። ይሁን እንጂ፥ 'እገሌ በሥጋ ይገለጣል' ወይም ይደበድበኛል ተብሎ ስሕተትን መንገር አይቀርም። ሲያሔሱ እንዲህም አለ።

ይድረስ ለዘማሪዎች ቁጥር 3ን ሌሎች እንዲሠሩት እያበረታታሁ ነኝ። ግን በቀደም ስለሰማሁት አንድ መዝሙር አንድ ልበል። 'ተነሺና አብሪ' የሚል ስለ ኢትዮጵያ የተዘመረ መዝሙር ነው። ደጋግሞ፥ 'የከፍታ ዘመን ሆነልሽ' ስለሚል ምናልባት 'የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ' ለተባለው ቪዲዮ ማጀቢያ የተሠራ ሳይሆን አይቀርም ብየ ገመትሁ። ተነሺና አብሪ ቃሉ ከኢሳ. 60 የተወሰደ ሆኖ ስለ ጽዮን የተነገረው ግን ስለ ኢትዮጵያ ተመንዝሮ የተዘመረ መሆኑ ነው።

Page 11: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

11

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

እዚህ መዝሙር ውስጥ የአፍሪቃና የአውሮጳ፥ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ክብሯን እንዳዩት ተዘምሮ (መቼ እንዳዩት ባይታወቅም በኃላፊ ጊዜ ነው የተዘመረውና ታይቷል ማለት ነው)፥

የናቁሽ ሁሉ የተጠየፉሽ ጊዜው ሲመጣ ይኸው ሰገዱልሽ . . .

የሚል ስንኝ አለ። ሰዎች መጥተው ለኢትዮጵያ መስገዳቸው እየተደነቀ ነው የተዘመረው። ለአገር የሚሰግዱ ሰዎች መልካም እንዳደረጉ ተደርጎ ነው የተዘመረው። ይገርማል! ሰዎች ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአገር (ለሳር፥ ለቅጠል፥ ለዛፍ፥ ለወንዝ፥ ለደብር) ሲሰግዱ ተደንቆ መዝዘመሩ። ስግደት የሚገባው አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና እንዲያው ቢሆን ኖሮ እንኳ እኮ ይህ በራሱ መወገዝ የነበረበት ነገር ነው። ግን በክርስቲያን ዘማሪ ነው የተዘመረው። ይህ ምኞት ይሁን ቅዠት አይታወቅም። እውነት ግን አይደለም። ጠቅላላ ስነ መለኮቱ የተሳሳተ መዝሙር ነው። አገርንና ሕዝብን መውደድ አንድ ነገር ሆኖ ያንን ማምለክ ግን ሌላ ነገር ነው። ይህ ለኢትዮጵያ መስገድ የጣዖት አምልኮ ነው!

ይህንን ኢትዮጵያን የተመለከተ የተዛባ አስተሳሰብ ከዚህ በፊት ሲል ጽፌአለሁ። ይህን የተዛባ ብቻ ሳይሆን ያበጠ አመለካከት ነው። አገርን መውደድ አንድ ነገር ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስነ መለኮት እስኪንኮታኮት ድረስ በምድራዊ አገር ፍቅር መስከር አርበኝነት ሊሆን ይችላል ክርስትና ግን አይደለም። ይህ ውሸትም ስሕተትም አለበት። መጥተው የሰገዱላት ስለሌሉ ውሸት ነው። ለአገር መስገድ ደግሞ ስለሌለባቸው ለአንድ ክርስቲያን ይህንን መዘመር ደግሞ ስሕተት ነው። ስሕተት ደግሞ ዝም ካሉት ይዘምማል፤ ያዘምማል። ስለ ዝማሬዎቻችን እንዲያው ናሙና ብቻ አሳይቶ ለመተው ያህል እንጂ የመዝሙሮቻችን ጉድፉ ተዝቆም አያልቅ።

ከላይ እንዳልኩት መዝሙሮች እየተንደረደሩ ሲወድቁ ዝም መባል የለበትም። በይድረስ ለዘማሪዎች ቁጥር 1 እና 2 መካከል (November 2008) አዲስ አበባ ተደርጎ በነበረ የመዝሙሮች አካሄድ ዐውደ ጥናት ላይ ያቀረብኩትን የኔን ጽሑፍ የደመደምኩት አራት ነጥቦችን በማሳሰብ ነበር፤ ሀ) ዘማሪዎች ጠንቃቃ ይሁኑ (ሲደርሱ፥ ሲያርሙ፥ ሲያገለግሉ፥ ሲያሳትሙ፤ ሌሎች ተሳታፊዎችና አድማጮችም በዚህ ቢተጉ)፤ ለ) የሕያሴ መዝሙራት ባህል ቢዳብር፤ ሐ) እንዲህ ያለው መድረክና ዐውደ ጥናት ቢለመድ፤ መ) ቢቻል አንድ ደረጃ አስጠባቂ አካል ቢኖር የሚል ነበር። እዚህን እዚህም ልደግም ወደድሁ። እንዲያው እንዲስተዋሉ።

በሥልጣን ጋሻና ዋሻ ውስጥ ቀደም ሲል ለመታረም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ሥራ አደባባይ ከወጣ በኋላ ግን ሕያሴ ቢደረግበትና 'ተጠየቅ' ቢባሉ መደንገጥና ወደ ዛጎላቸው ውስጥ እንደሚገቡ ወይም አግጥጦ ለመናከስ እንደሚወጡ ብዬ ነበር። አንዳንዶች ሁለቱንም አያደርጉም፤ ወደ ዛጎልም አይገቡም፤ ወጥተውም አይናከሱም። ግን መከላከያ እርድ ያደርጉና አትድረሱብን ይላሉ። ዋና ጥቅስ አላቸው፤ የቀባኋቸውን አትዳስሱ፤ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ፤ 1ዜና 16፥21-22 እና መዝ. 105፥14-15። እንዲያው በመልካም የሚዳሰሱ ቢሆኑ እንኳ ደግ ነበር፤ ተዳስሰው የሚወጣቸው ከኖረ። ጌታን እንዳጋፉትና እንደዳሰሰችው። እነዚህ ከመደዴው አማኝ እየራቁ 'ጨርቃቸውም ጥላቸውም' የማይደረስበት ሆኑ።

አሁን እየበዙም እየናሩም ያሉ የመሰሉ፥ ግን እየረከሱ የመጡ ሥልጣኖች አሉ፤ ሐዋርያ እና ነቢይ የሚባሉ። ሐዋርያና ነቢይ ጸጋ ነው ወይስ ማዕረግ እያሉ የሚከራከሩ አሉ። ለተከራካሪዎቹም ሆነ ለሰዎቹ ለራሳቸውም ሁለቱም ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ሌላ ሦስተኛም አለ፤ ሥልጣን። ዋናው እንዲያውም የጸጋና የማዕረግ ጉዳይ ሳይሆን የሹመት ጉዳይና የሥልጣን ጥም ነው። አንዳንዶቹ ለሥልጣን እስከ ቄሣር ለመሄድ ግድ የላቸውም። ደግሞም በዙሪያቸው ያሉትንም እየደፈጠጡ ነው የሚሄዱት። ለአገልግሎት ሳይሆን ለሥልጣን።

ብዙዎቹ በማንም ያልተሾሙ ናቸው። አንዳንዶች ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ ናቸው። የራሱን ዘውድ በገዛ እጁ እንደደፋው ናጶሊዎን። ስለ ሕዝብ ሰው በጻፍኩት አንድ መጣጥፍ ይህን ጠቅሼዋለሁ። እርስ በርስ እንደዚያ (ሐዋርያው እገሌ እና ነቢዩ እገሌ) እየተባባሉ በመጠራራት ያባዙታል። ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኖችና በአማኙ ማኅበረ ሰብም ማዕረጉ ይጸድቃል። በኤፌ. 4፥11-12 ያለው እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ የሚል በሐዋርያት ጀምሮ በአስተማሪዎች የሚጨርሰው ዝርዝር መነሻ ነው የብዙዎች ቀልብ የተወሰደበት።

ሐዋርያትና ነቢያት ላይ ያለው ትኩረት አዲስ የሐዋርያትና ነቢያት መሠረት እየተጣለ ያለም አስመሰለው። ቤተ ክርስቲያን ቀድሞውኑ በነቢያትና ሐዋርያት መሠረት ላይ ከተመሠረተች (ኤፌ. 2፥19) ይህ ለምን እንዳስፈለገ አይናገሩም። ሐዋርያው እና ነቢዩ ላይ ብቻ እየረገጠ የወንጌል ሰባኪዎችጋ ሲደርስ መቆሙ ግን ያሳዝናል። ይህኛው ወንጌሉንም እንዳይሮጥ አስቆመው። ለዚህ ነው እግራቸው እስኪቀጥን ቢሄዱ ቢሄዱ ወደ ደረጁ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የሆነው። 'በየኮንፈረንሱ' ደግሞ ሌላው ግርግር ሁሉ ሲደረግ ላልዳኑ የሚሆን ወንጌል በግልጽ አይስበክም። ለዳኑትም በወጉ ትምህርት አይሰጥም። ጳውሎስ በአቴና እንደሆነው በሚያዩትና በሚሰሙትም መንፈሳቸውም አይበሳጭም። ወንጌልና ትምህርት እየከሳ፥ ያልተላኩ ሐዋርያትና ቃሉን የማይገልጡ ነቢያት እየወፈሩ መጡ። ወንጌል ወዳልደረሰበት መሄድማ ጨርሶም የማይታሰብ ጉዳይ ነው። ከቃሉ ይልቅ በሕልም በራእይና በመገለጥ እየተደገፉ፥ ይህንንም ቢያንስ ከቃሉ እኩል ሥልጣን በመስጠት አንዳንዴም በማስበለጥ ጫናቸውን በአማኙ ጫንቃ ይቆልላሉ።

'መገለጡ' ፍጻሜ የሌለው ነው። በግምትና በነሲብ የተሞላ ቢሆንም እንኳ ሳይፈጸም ለሚቀር ነገር ተጠያቂ ላለመሆን (ወይም ተቀባዩን ተጠያቂ ለማድረግ) የማይመዝዙት ሐረግ የለም። ይህን እየጻፍኩ ሳለሁ (Sepember አጋማሽ 2014) የቲ. ቢ. ጆሹዋ ቤተ መቅደስ ሆስቴል በውስጡ ካሉት 200 ያህል ሰዎች ጋር ተደረመሰ። በመጀመሪያዎቹ 3 ቀናት ከ80 ሰዎች በላይ እንደሞቱ ተረጋገጠ። ከወር በኋላ ቁጥሩ ከ115 አልፎአል። ከ80 የሚበልጡቱ ደቡብ አፍሪቃውያን ተሳላሚዎች ናቸው። አንድ የእግር ኳስ ቡድን እንደሚያሸንፍ፥ የሆነ ደሴት ላይ አውሮፕላን እንደሚወድቅ፥ የሆነ አገር የምርጫ ተወዳዳሪ እንደሚያሸንፍ፥ የሆነ ታዋቂ ሰው እንደሚሞት (ከሞተ በኋላ ማይክል ጃክሰን እንደሆነ የተናገረው)፥ ወዘተ፥ 'ያየውና የተነበየው' ቲ. ቢ. የSCOAN ቤተ መቅደ ሆስቴል ሲፈርስና ይህን ያህል ሰዎች በውስጡ ሲሞቱ አላየም፤ አልተነበየም። 'ምነው?' ቢባል መልሱ የሌሎቹንም ግምትነት ሊያረጋግጥልን አይችልም?

የቲ. ቢ.ን ትንቢቶች በአጋጣሚ ሕግ እንኳ ብንመለከት አንድ ቡድን የማሸነፉ ዕድል 50% ነው። ደግሞም አንድ የእግር ኳስ ቡድን አሸነፈ፥ ተሸነፈ ለጌታ መንግሥት የሚፈይደው ነገር ምንድር ነው? አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ የታወቀ ሰው ወይም ዘፋኝ በአንድ ዓመት ውስጥ የመሞቱ እርግጥነት ደግሞ ከ100% በላይ ነው። (የማይክል ጃክሰን ስም የተጠቀሰው ከሞተ በኋላ ነው እንጂ በትንቢቱ ውስጥ አይደለም)። ስለ ሆስቴሉ መፍረስ በሌጎስ ስቴት መንግሥት የተረጋገጠው መግለጫ የሕንጻው መሠረት ከሚችለው ከሁለት ደርብ በላይ አራት ፎቆች፥ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ መገንባታቸው ሲሆን ቲ. ቢ. የተናገረው ግን የሆነ አውሮፕላን በሕንጻው ላይ አንዣብቦ የሆነ ነገር ስለረጨ ነው የሚል ነው። ኋላ የረጨው ነገር ሳይሆን ድምጹ አንቀጥቅጦት ነው ተባለ። መጀመሪያ ቦኮ ሃራም የተባለውን አክራሪ እስላማዊ አንጃም እንደ ምክንያት አድርጎ አቅርቦ ነበር። ለሕንጻ ጠበብት ግን ይህ የማይመስል ምክንያት ነው። አንዳንዶች ይህ controlled demolition ነው ብለዋል።

የናይጄሪያ ባለ ሥልጣናት የሚሉትን ገና ተሠርቶ ባላለቀ ሕንጻ ሰዎች እንዲገኙበትና እንዲቆዩበት፥ እንዲመገቡበትና እንዲያድሩበት ማድረግ ከሕግ የወጣ ሥራ መሆኑን አልተቀበለም። በዘመናችን ነቢያትና

Page 12: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

12

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ሐዋርያት ዘንድ ስሕተት ተቀባይነት የለውም። ከስሕተት በላይ እንደሆኑ ራሳቸውን ስለሚያዩና ስለሚታዩ። ገና የሰዎቹ ቁጥር በውል ባልታወቀበትና ቁጥሩ እየጨመረ ባለበት ከመፍረሱ ቀጥሎ ባለው እሁድ ባደረገው ንግግር ዒላማው እርሱ እንደሆነ በመናገር ስለሞቱት ሰዎችና ቤተሰቦች ያለው ነገር ግን አልነበረም። አንድ ቀድሞ የመቅደሱ አገልጋይ የነበረና ኋላ የተለየ ሰው፥ "የዚያ እሁድ አምልኮ መደረጉ ራሱ ለሚዲያ እንጂ ለአምልኮ አለመሆኑን ያረጋግጣል" ብሏል።4 ከአቅራቢያ ከተቀረጸ የሴኪዩሪቲ ቪድዮ እንደታየው አውሮፕላኑ በመጨረሻ ከበረረ ከ50 ደቂቃ በኋላ ነው ሕንጻው የተደረመሰው። የሞቱትን ሰዎች ሰማዕታት እና የእምነት አርበኞች የሚላቸው ቲ. ቢ. ስሕተቱን ወድዶ ለማመን ግን ገና ትንቅንቅ ሆኖበታል።

ሰዎች ወደ ላይ ሲወጡ ዋና ችግራቸው ስሕተትን አልፈውት የወጡ፥ መሳሳት የሚአል ነገርን ተራምደው ያለፉት መምሰሉ ነው። በአገራችን ሰዎች እየተነዛ ያለው የነቢያትና ሐዋርያት ማዕረግ፥ ሹመት ወይም ሥልጣን በእነርሱ የተጀመረ አይደለም። በምዕራቡ ዓለም፥ በተለይ በአሜሪካ እየተወለደ እያደገ እየሞተ፥ በፈንታው ሌላ እየተወለደ ያለው የተሐድሶና መነቃቃት ንቅናቄ አካል ነው። የንቅናቄው ጉልህ መሪዎች ይህንን የሐዋርያዊ እና ነቢያዊ አገልግሎት ዳግም ምጽአት ወይም መመለስ ይሉታል። እነዚህ ሰዎች የመጠቁ፥ የማይደረሱ፥ የማይነኩ፥ የማይስቱ፥ የማይሳሳቱ፥ የማያሳስቱ ሆነው እየታዩ፥ ቃላቸው ቃሉ እየሆነ የመምጣት አዝማሚያ ተጀምሮአል። ከሕያሴ በላይ ሆነው በትንቢትም ያለ ትንቢትም ማስፈራራትም ጀምረዋል።

ከዶሚኒየን ቲዮሎጂ ወይም መንግሥታሁን (መንግሥት አሁን) የሚባለው የስሕተት ትምህርት አስፋፊዎች አንዱ የሆነው ሪክ ጆይነር አዲሶቹን የሐዋርያትና ነቢያት ትውልድ 'ሱፐር ነቢያት እና ሱፐር ሐዋርያት' በማለት ሲሰይማቸው ሐያሲዎችን ወይም ይህን ንቅናቄ የሚሞግቱትን ደግሞ፥ ፈሪሳውያን ይላቸዋል፤ ደግሞም 'በሃይማኖት መንፈስ እና በኤልዛቤል መንፈስ የተመሩ' ይላቸዋል።5 ሪክ ጆይነር የሚያሔሱ ወይም ስሕተትን የሚያጋልጡ ሰዎች አእምሮአቸው በዚያ በሚያጋልጡት መንፈስ የጨለመ ነው ይላል። ደግሞም፥ የስሕተት አስተማሪዎችን ስሕተት መግለጥ በጨለማ መመላለስ ነው ይላል።6 ማስፈራሮው ቀላል አይደለም። ለዚህም ነው በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ሐያሲነት ለፈሪ አይሆንም ያልኩት። ማስፈራራቱ አንዳንዴ በትንቢት ቃል መርገምን መላክም ይሆናል። ቤኒ ሂን ከጥቂት ዓመታት በፊት ሐንክ ሐነግራፍ የተባለውን ሐያሲ እርሱ ለሚያሔሰው ነገር ልጆቹ ዋጋ እንደሚከፍሉ በመናገር ሊያስፈራራ ሞክሮ ነበር። የዛቻውን ቃል በሬድዮ ሲያስተላልፍ ሰምቼዋለሁ።

ጥቂት እንዳላሔስ በልስላሴ የሚመክሩኝ ወንድሞች አሉ። ከነዚህ የአንዳንዶቹን 'ቅን ፍርሃት' ልበለው። ሒስ መንፈሳዊ ሕይወቴን እንደሚያበላሸው መፍራታቸው እንደሆነ ነግረውኛል። ስጋታቸው መልካም ሆኖ አመለካከቱ ግን ትክክል አይደለም። ጠርጣሪና ጠያቂ ሁሉ መንፈሳዊነት የጎደለው ነው ማለት ትክክል አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ የተሰጠውን ሁሉ ያለጥያቄ የሚበላ ሁሉ መንፈሳዊነት የበረከተለት ሰው ነው ማለትም ስሕተት ነው። ከዚህ በፊት በአንድ መጣጥፍ የጠቀስኩትን ታሪክ ልድገም፤ አንድ ጓደኛዬ ያልተለመዱ ምግቦችን መቀማመስ ለምዶ አንዱን የወደደውን ምግብ ለሌሎችም መጋበዝ ጀመረ። አንድ ቀን አንዱን ወዳጁን ከጋበዘውና የተጋበዘውም በሳህኑ ላይ ምንም እስከማይተርፍ አጣጥሞ ከበላና ከጨረሰ በኋላ የበላው የእንቁራሪት እግር መሆኑን ነገረው። ለአንዳንድ አገር ሰዎች ይህን መብላት ማለት ለአበሻ የዶሮ ሥጋ ወጥ እንደመብላት ያህል ነው። ይህ ተጋባዥ ግን

4 http://tbjoshuawatch.wordpress.com/category/news/ 5 http://www.pfo.org/r-joyner.htm 6 http://www.apologeticsindex.org/j08.html

ፈረንሳዊ ሳይሆን አበሻ ነውና ከልቡ ነበር ያዘነው። ሳንጠይቅ በልተን ኋላ ቋቅ ከሚለን የሚበሉትን መጠየቅ አግባብ ነው።

የሌሎቹ ወዳጆቼ 'እረፍ!' ማለት ግን ቅን ፍርሃት ሳይሆን፥ የማሔሰው ነገር ስሕተት መሆኑን ሳያውቁት ቀርተውም ሳይሆን የራሳቸውን ፍርሃት ማስተጋባታቸው ነው። ወቀሳ ባለበት አካባቢ መገኘት ጭንቃቸው ስለሆነ ነው። እንዲህ ካሉቱ መካከል አንድ አገልጋይ ስለ አንድ ነገር ለምን እንደጻፍኩ ጠየቀኝ። እኔም ያ የጻፍኩበት ጉዳይ መታረም የተገባው ስሕተት መሆኑን እንደሚያምን ወይም አንደማያምን ጠየቅሁት። ስሕተት መሆኑን እንደሚቀበል ነገረኝ። "ታዲያ ስሕተትነቱን ካመንክበት አንተ መናገር ወይም መጻፍ ነበረብህ፤ ካልሆነ ደግሞ አንተ ለመጻፍ ስለፈራኸው ጉዳይ የሚጽፍ ከተገኘ ደስ ሊልህ ይገባ ነበር እንጂ ለምን እንዳይነገር ፈለግህ?" አልኩት። መልሱ የሰነፍ መልስ ሆነብኝ። የአንዳንዶች ፍርሃት ሌሎችን ለመታደግ ይመስላል እንጂ ጉዳዩ ጭራሽ በአካባቢያቸውም አንዳይነሳና 'ተኩሱ' ባይነካቸውም እንኳ በጆሮአቸውም ላለመስማት የመስጋት ጉዳይ ነው። 'አልደርስብህም አትድረስብኝ' ማለት ለራስ ለሚቆም ሰው ሊመች ይችላል። ግን ለሌላው ሊጠነቀቅ ግድ ለሚለው አይመችም። ይህም የሐያሲ 'ጣጣ' ነው። ሕያሴ 'ተኩስ' ሲሰማ ለሚበረግግ አይመችም።

በልስላሴ መምከር ብቻ ሳይሆን በኃይለ ቃልም ሊያስደነግጡ የሚሞክሩ አልጠፉም። አንድ በዕዝራ ላይ የጻፍኩት ሕያሴ ያበሳጨው ወንድም እንደሚከስሰኝ ዝቶብኝ ነበር። ዛቻውን አልፈራሁም። በተለዋወጥናቸው ኢሜይሎች ስድብም ተደባልቀውበታል፤ ያ አያንጽምና ልተወው። በአንዱ ውስጥ፥ Let me remind you in this country with out getting permission from the other party when you become UN-brotherly or unfriendly critic that will lead you to litigation with a great evidence in hand individually and corporately. አንድ አራቴ ያህል ከተጻጻፍን በኋላ ቢከስሰኝ በኔ ላይ ከሚሆነው ምናልባት ራሱ የሚጠየቅበት እንደሚያይል ተረድቶ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት አላውቅም፤ የተወው መሰለኝ። ወይም አልተወውምም ይሆናል። እንደዚህ ወንድም ከላይ የጠቀስኩት አባባል ሒስ ለማቅረብ መጀመሪያ ማስፈቀድም ያስፈልጋል፤ ሰውየው ካልፈቀደ አይወቀስም ማለት ነው። ስለዚህ ሕያሴ የሚሉት ነገር በአፍጢሙ ይደፋ! ስለማይፈቀድ አይቻልማ! ማን ነው፥ 'አሒሰኝ' ብሎ የሚፈቅድ? ጥሩነቱ ግን፥ የኅሊናና አሳብን የመግለጥ ነፃነት እስካለ ድረስ፥ 'ላሒስህ?' ብሎ የመጠየቅና የፈቃድ ወረቀት የማውጣት ግዴታ አለመኖሩ ነው። ማስፈራሮው ግን ቀላል አይደለም።

ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዲያዝንብን አንፈግልም። ቃሉን ካላወቅን ደግሞ እርሱን አናውቀውም። ሌሎች አውቀውልን ቃሉም አሳቡም በነዚያ ሰዎች ብቻ እንዲመጣልን በራሳችን ፈርደን ከወሰንን የሰዎች ስሕተት ውስጥ እንወድቃለን። ሰዎቹ ፍጹማን ስላይደሉ። አንዳንዶቹ 'ነቢያትና ሐዋርያት' በራሳቸው አጀንዳ የተቀቡና ወደ ግባቸው የሚሮጡ ናቸው። ስለዚህ በመንገዳቸው የሚቆም፥ ሥልጣናቸውንና ትምህርታቸውን የሚጠይቅና የሚጠራጠር መኖር የሌለበት ይመስላቸዋል። ራሳቸውን ከተጠያቂነት በላይ አድርገው የማይደረስበት ግንብ ሠርተው ወጥተውበታል።

Page 13: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

13

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ከላይ በዚህ ንዑስ ርእስ መግቢያ ያልኩት የተቀቡትን አትዳስሱ ማለት የማይጠየቁና የማይፈተሹ መሆን ነው? ደግሞስ ጥቅሱ ያንን ይናገራል? አትዳስሱ እና ክፉ አታድርጉ በተጻፈበት ዐውዱ ሲታይ ስለ ወቀሳና ሒስ አለመናገሩን፥ እነርሱም የማይሳሳቱ አለመሆናቸውን ለማየት አይከብድም። የብዙ አገልጋዮች የስሕተት ትምህርቶች ዋና መነሻ ዐውድን አለማጤን ነው። ጥቅስን ከስፍራው ነቅሎ ለብቻው መስበክ ነው። አብዛኞቹ ይህን በመጀመሪያ ሳያስተውሉ ነው የሚያደርጉት። ወይ ከመረዳት ማነስ፥ ወይ ከአጠናን ጉድለት፥ ወይ በመጀመሪያ የሰሙትና የተማሩት እንደዚያ ስለሆነ፥ ወይም አንዴ የተናገሩትን በመድገምና እንደ ስሕተት ላለመቁጠር በመከላከል ይሆናል። ይህኛው የመጨረሻው ወደ እልከኝነት የሚወስድ ልምምድ ነው። ትምህርታቸው ትክክል እንዳልሆነ ሲነገራቸው ከመስመር ይወጣሉ። ወይ ሽሽት ወይም በኃይልና በማስፈራራት መምጣት ይኖራል። ትክክለኛው መንገድ ግን ስሕተት ከሆነ መታረም፤ ስሕተት ከነበረ ደግሞ መጸጸትና ስሕተትን መቀበል ነው። የአትንኩን ባይነት ሽሽት ወደ ሹመት ጎጆ ውስጥ ገብቶ መደበቅንም ይይዛል። እገሌ የተቀባ ሐዋርያ፥ ነቢይ፥ የእግዚአብሔር ሰው ነው እየተባሉ።

የነዚህ ዓመታት ነቢይነትና ሐዋርያነት ከጸጋ ስጦታነት ይልቅ ማዕረግና ሹመት ሆኖ እየታየ ነው። ብዙዎች የሚመስላቸውም እንደዚያ ነው። ጸጋ ሳይሆን ማዕረግ ከሆነ መለኪያው ምንድርነው? የሚደረስበት በዕድሜ ነው ወይስ በአገልግሎት ዘመን? ማዕረግ የሚገኘው እንደዚያ ነው። አንድ ወታደር በትክክለኛው ሂደት በወራት ውስጥ ጀነራል ለመሆን አይችልም። 40 ዓመት አገልግሎ ሐዋርያ ከተሆነ እውነትም ማዕረግ ይመስላል። እንደ ሙሴ 80 ያገለገለስ ከኖረ ምን ሊሾም ይሆን? በ4 ወራቸው ሐዋርያው እገሌ የሚባሉት የተቀዳጁት ማዕረግስ 'ሜድ ኢን ቻይና ሐዋርያ' ልንለው ነው?

በአንድ መጽሔት ላይ "በኢትዮጵያ አንድም ቢሾፕ የለንም" አሉ ዶ/ር ቶሎሳ።7 የቁጭት ይመስላል አባባሉ። ቢሾፕ ያሉትን በአማርኛ ቢሉት ኖሮ መኖር አለመኖሩን ስለሚያሳየን መልካም ነበር። ወይስ ቢሾፕ የሚሾሙ እንደ አንግሊካን ያሉ አብያተ ክርስትያናት አገራችን የሉም ማለታቸው ይሆን? ወይስ ሪክ ጆይነር እንደሚላቸው ያሉትን 'ሱፐር ሐዋርያት' ማለታቸው ነው? እንዲያው ለጉዳዩ፥ በወንጌል ሽታ ለታጠነችውና ግን ክርስቶስን በማያሳዩ ሃይማኖቶች ለተሞላችው አገራችን የሚያስፈልጉን ቢሾፖች ናቸው ወይስ የወንጌል ሰባኪዎች? ቢባል መልሱ ግልጽ ነው። 20 ሚሊዮን ነፍሳት (አሁን ያለው የወንጌላውያን አማኞች ቁጥር) የተደረሰው ያለ አንድ ቢሾፕ መሆኑስ አያስገርምም? ቢሾፕ ተብሎ በእንግሊዝኛ የተተረጎመው የአዲስ ኪዳን ቃል ኤጲስቆጶስ የተባለው የግሪክ ቃል ነው። የቃሉን ትርጉም ደግሞ በጣም ከፈለፈልነው ከላይ ሆኖ የሚመለከት ማለት ሆኖ በጥቅሉ ግን የሚጎበኝ የሚያይ ማለት ነው። በቀላሉ እረኛ ማለት ነው። እነዚህ የሉንም ማለት ነው? አንድም?

መልክና ማንነት እየተራራቀ በመጣበት ጊዜ ላይ ነን። በዚህ ዘመን ማስታወቂያውና እውነቱ እየተራራቀና እየተለያየ መጥቶአል። ስለዚህ ፎቶውንና ነገሩን ማስተያየት የግዴታ እየሆነ መምጣት አለበት። ዱሮ በአገራችን 'የእጅ ሥራ ፎቶ' ይባላል። ከሲታውን ሰው ጉንጫም፥ ከርዳዳውን ጠጉር ዞማ፥ ጥቁሩን ጠይም፥ ሌላም ሌላም ያደርጉታል። በቀደም Pinnacle Studio የሚባል ሶፍትዌር ገዛሁና ከፍቼ ስሠራበት የዱሮውን የእጅ ሥራ ፎቶ የሕፃን ጨዋታ እስኪመስል የሚያስንቅና የሚፈጥራቸው ትንግርት የሆኑ ነገሮች ይገርማሉ።

አንድ ፎቶግራፊ እና ፎቶ ጆርናሊዝም የተባለ ኮርስ ያጠና ማርቆስ የሚባል ጓደኛ አለኝ። ማርክ ለምረቃ የሠራው ዋና የጥናቱ ፕሮጄክት የፈጣን ምግብ ቤቶች ምግቦችን ማራኪ አድርጎ ፎቶ በማንሣት

7 ካቦድ፥ ቁጥር 4፤ 2001 ዓ. ም. ገጽ 21።

ለማስታወቂያ ማቅረብ ነው። የሚያነሣቸው ፎቶዎች ምራቅ የሚያስውጡ ናቸው። ይህ የፎቶ አንሺው የማርክ ሥራ ነው። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ በዚህ ዓመት በበጋው ወራት የተደበቀ ካሜራ በመነጽሩ ውስጥ ቀርቅሮ እንዲህ ያሉ ፎቶዎችን የሚያስተዋውቁ ምግብ ቤቶችን እያደነ የማስታወቂያውን ፎቶዎች ከቀረበለት ምግብ ጋር እያስተያየ ያሳፍራቸው ነበር። የጥቂት ደቂቃዎች ቪድዮ ነው። ለማየት ከግርጌ ያለውን የዩቲዩብ ክሊፕ ተመልከቱ።8 ካስተያያቸው መካከል አንዱ ይህ ነው። ፎቶው ምናልባት ጓደኛዬ ማርክ ራሱ ያነሣው ሳይሆን ይቀራል? የሁለቱ ልዩነት በጣም ግልጽ ነው።

በዘመናችን እየሆነ ያለው ይህን ይመስላል። ባንዲራው ይውለበለባል፤ ምርኮኛው ግን ብዙ ነው። የኮንፈረንሶችን ማስታወቂያዎች ማንበብም ከዚህ ጋር አንድ ሆኖአል። የምግቡ ማስታወቂያና ምግቡ የተራራቁ እንደሆኑ ማስታወቂያውና የሚታየውም ለየቅል ናቸው። ይህን እየጻፍኩ የአገልጋዮች ማስታወቂያዎች ምን እንደሚመስሉ ለማየት የWongelnet.comን ማስታወቂያዎች ማንበብ ጀመርኩ። ከዚህ በፊት የሚያስቁ ማስታወቂያዎችን አንብቤ ስለነበር ነው ወደዚያ ጎራ ያልኩት። እዚያ ሁሌም የሚገርም ነገር አይጠፋም። ሳነብብ አንድ የኛም ቤተክርስቲያን የተጠቀሰችበትን ማስታወቂያ አየሁ። ማን እንዳስለጠፈው አላውቅም፤ ግን የኛም ቤተ ክርስቲያን ስላለችበት የመጥቀሱን ነፃነት መውሰድ አልከበደኝም። Earth shaking revival with the sprit and the word of God ይልና Come join Us The Holly Spirit is on duty to serve you and meet your needs ይላል።

የእንግሊዝኛውን ፊደል አቀማመጥ (እስፔሊንግ) ሳላርም እንደተጻፈው ነው የጻፍኩት። sprit እና Holly በጣም የሚያናድዱ አጻጻፎች ናቸው። አንዷ ከተማ Lethbridge የምትባለው Last Bridge ተብላለች። በመጀመሪያ የአማርኛ አገልግሎት ሆኖ ለምን በእንግሊዝኛ ማስታወቂያ እንደሚጻፍ ግራ ነገር ነው። ከተጻፈም ምናለ ጠንቃቃ ሰው ቢጽፈው? ባለ ድረ ገጹስ ማረም የማይችል ከሆነ ለምን አያሳርምም? ሁለተኛው የማስታወቂያው ይዘት ነው፤ 'ምድር የሚያናውጥ revival' ተብሎአል። እውነት አይደለም፤ ምድር አልተናወጠችም። ደግሞም፥ 'መንፈስ ቅዱስ ሊያገለግላችሁና ፍላጎታችሁን ሊፈጽም ቆሞ እየጠበቃችሁ ነው' ተብሎአል። (የራሴ ትርጉም ነው፤ ግን ትክክል ነው) ይህ ምን ማለት ነው? መንፈስ ቅዱስ ፈቃዳችንን እና ፍላጎታችንን ልናስገዛለት የተገባው አምላክ ነው ወይስ ምኞታችንን ሁሉ ለመፈጸም ታጥቆ የሚያገለግለን አገልጋይ? አገልጋዩ ዘመድ ሊጎበኝ እከተማችን በቆየበት ጊዜ አብረን ጊዜ አሳልፈናል፤ ማኅበራችንንም አገልግሎአል። ማስታወቂያውን ኋላ የው

8 http://www.youtube.com/watch?v=XrZFM2nvLXA

Page 14: ቁጥር ፳፯ ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014 ቁጥር ፳፯cdn.good-amharic-books.com/EzMag027.pdfእህሉን ወደ ውስጥ ይሰበስባል።

14

ቁጥር ፳፯ - ጥቅምት ፪ሺህ ፯ ዓመተ ምሕረት OCTOBER 2014

ያየሁት፤ የራሱ አይደለም። ግን በማስታወቂያና በፎቶው የሚታየውና በገበታው ላይ የሚቀርበው ከተለያዩ መጠየቅ የለበትም?

ኧረ ይጠየቃል! በዚህ ዘመን የሚሆነውን ስናጤን እውነትም ሰው ተገልጋይ እግዚአብሔር አገልጋይ የሆነበት ዘመነ ግርምቢጥ ነው። ብልጽግና ይሰበካል፤ ትጋት፥ ታታሪነትና ሠራተኝነት ግን አይነኩም። ድሎት፥ ምቾት፥ ጤንነት፥ ወዘተ፥ ይሰበካል፤ እነዚህ ሳይሆኑ ቢቀሩ ወይም ተቃራኒው ከሆነ ዝግጁ የመሆኛው መንገድ ግን አይነገርም። ለፈተና ወይም ለስደት ዝግጁ እንድንሆን ሳይሆን ከነዚህ ነገሮች የጸዳን መሆናችን ይነገረናል። በመከራ መጽናት አይሰበክም። እና ሰዎች በመከራ ውስጥ ሲያልፉ ከራሳቸውም ከእግዚአብሔርም ጋር ጥለኞች ይሆናሉ። የሌለ ፈውስ ይሰበካል፤ ፈውስ ከሌለ ኮንፈረንስ እንደከሸፈ ስለሚቆጠር። ፈጽሞ የሌለ ፈውስ ይታወጃል! ይህ ቢጠየቅ ለምን ይገርማል?

ፈውስን ካነሣሁ አንድ ልበል። በጣም የታወቁ አራት (ስማቸውን በዚህ ጽሑፍ ልለፈው ግን በጣም የታወቁ) የአገራችን አገልጋዮች በተአምራት አገልግሎቶቻቸው ስለፈወሷቸው ሰዎች የተናገሩትንና የጻፉትን በመጥቀስ አራቱንም ማረጋገጫ እንዲሰጡኝ ጠየቅኳቸው። እመኑኝ፤ በእግዚአብሔር ፈዋሽነት አምናለሁ። የፈውስ ስጦታም ዛሬም እንዳለና የፈውስ ስጦታ ባላቸው ክርስቲያኖች (የግድ የታወቁ አገልጋዮች መሆን የለባቸውም) ወይም በሽማግሌዎች ዘይት መቀባትና ጸሎት ፈውስ እንዳለ ቃሉን እቀበላለሁ። ከአራቱ የመጀመሪያውን ከጠየቅሁ 10 ዓመት አልፎታል። እንኳን ሊመልስ እንደተጠየቀም እንኳ የቆጠረው አይመስለኝም። የመጨረሻውን አገልጋይ የጠየቅሁት በዚህ ወር (September 2014) ነው። እነዚህን ሁለቱን እና ሌላውን ሦስተኛውን ሰው ማረጋገጫ የጠየቅኋቸው ሦስቱም ፈውሶች ከኤች አይ ቪ ኤድስ ስለሆኑ ነው። ከዚህ በፊት ከኤድስ ሳይፈወስ ተፈወሰ ብሎ በስሕተት ስላወጀ ሰው እና ተፈወስኩ ብሎ ስላጭበረበረ አንድ ሰው ጽፌ ነበር፤ ታስታውሱ ይሆናል።

ኧረ እንጠይቅ! እንዲህ ያለ ነገር ዝም አይባልም፤ ይጠየቃል። ይህን መጠየቅ እንደ ተግዳሮት መታየት አለበት? ከኖረበት፥ አዎን አለበት! ለሐሰተኞች ፈውሰኞች ተግዳሮት ሊሆን ይችላል። ለጠያቂዎች ግን መብት ነው። ስለጠየቅን እምነታችን አይጠፋም፤ ይረጋገጣል እንጂ። የሌሎቹም እምነት አይናጋም። ይህ እግዚአብሔርን መፈታተን ሳይሆን ሰዎቹን መፈተን ነው። ውጤታቸውን መፈተሽ ነው። መንፈስን መመርመር ነው። መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መርምሩ ነው የተባለው፤ 1ዮሐ. 4፥1። ሌሎችም የጠየቅኋቸው አሉ፤ ግን የዚህ ዓይነቱን 'ፈውስ' ማንሣት የወደድኩት አካላዊው ችግር ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግርም ስለሚወልድ ነው። በቀላሉ በሚያምን የዋኅ ማኅበረ ሰብ ውስጥ 'ተፈወሰ' የተባለ ግን ያልተፈወሰ የኤድስ ሕሙም ጤናማ ልጅን ሊያገባ ይችላል፤ ቢያገባ ውጤቱ ገሃድ ነው።

ምልክቶችና ተአምራት፥ ድንቆችና ፈውሶች የሚጠየቁበት ሌላ ዋና ምክንያት እነዚህ ነገሮች ራሳቸው፥ 'መርምሩኝ፥ ፈትሹኝ!' ብለው ስለሚጮኹ ነው። ተአምራት ሳይሆኑ ስለቀሩ ነው። በኢየሱስ ስም ተጸልዮለት ዕውር ቢያይ ማን ይጠይቃል? ሽባ እንደ ሚዳቋ ቢሮጥም እንደዚያው። በጌታ ስም ብረት ቢንሳፈፍ ማን ይጠይቃል? ፀሐይ ብትቆምም እንደዚያው። ዓይንሽ ተፈወሰ ተብላ መነጽሯን የጣለች እኅት ነበረች። ኋላ ደረጃ እንኳ ስትወጣና ስትወርድ ባሏ እስኪደግፋት ደረሰች። መጽሐፍ ቅዱሷን ማንበብ ስላልቻለችም አንባቢዋ ባሏ ሆነ። በኋላ ግን በሕክምና ዕርዳታ አጥርታ ማየት ቻለች። መነጽሯን የጣለችው ግን ተፈውሰሻል ተብላ ነበር። 'ፈውሶቹ' ራሳቸው፥ 'ኡ! ኡ! መርምሩን! እውነተኞች ነን ወይስ አይደለንም? ኧረ ፈትሹን!' እያሉ የማንመረምር ከሆንን ስሕተተኞች ነን።

ስለዚህ ፈውሰኞች መጠየቅ አለባቸው። ቢሆን ቢሆን ራሳቸውም ማረጋገጫ ማስመጣትም አለባቸው። ለአገልግሎታቸው ጤንነት ሲሉ። ከላይ የጠቀስኩት ሐንክ የተባለው ሰው ቤኒ ሂንን በእርግጥ ተፈወሱ የሚላቸውን ሦስት ሰዎችን ከማስረጃቸው ጋር እንዲሰጠው ጠይቆት ሦስት ሰዎችን ሰጠው። ሐንክም ቤኒ የሰጠውን ሦስት ሰዎች ተከታትሎ የሦስቱም ሰዎች ፈውስ እውነተኛ አለመሆኑን አረጋግጦ ነበር። ፈውስ በሰውነታችን የምናውቀው እውነታ እንጂ ስሜት አይደለም። ያቺ ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴት ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች ነው የተባለው፤ ማር. 5፥29። ፈውስ ከማን ይልቅ ለተፈዋሹ የሚታወቅ ነገር ነው። ከማንም ይልቅ የፈውሱን እውነትነትና ውሸትነት ማወቅና ካልኖረ የለም ማለት የእነርሱ ቃል መሆን ነበረበት። ግን ይህን ማለት ከቶም ያልኖረውን ፈውሳቸው የሚያሳጣቸው ተደርጎ ስለሚነገራቸው ሊሉት አይደፍሩም። ይህ እምነት ማጣት ነው ይባልባቸዋል። ባይሉትም እንኳ መድኃኒታቸውን አቁመው ለከፋ አደጋ ባይጋለጡ መልካም ነበር።

ሳይፈወሱ ተፈወሳችሁ ተብለው መድኃኒት ጥለው የማቀቁና የሞቱ ሰዎችን አውቃለሁ። ይህ ብቻውን እንኳ እየጮህኩ እንድናገር ሊያስገድደኝ የተገባ ነው። ፈውሰኛው ተናግሮ ይሄዳል፤ ሕሙማኑ ሲማቅቁ አይሰማቸውም፤ አያያቸውም። 'ሳያምኑ ቀርተው ወይም እምነት ጎድሎአቸው ነው' የሚሉትን የወረደ አባባላቸውን መሸፈኛ ማድረጋቸውን ወደ ጎን ትተን የራሳቸውን ኢተጠያቂነት ለመጠየቅ ድፍረታችንን በማስፈራሮ ሊተበትቡና ሊያስተበትቡ ይጥራሉ። የለም፤ ይህ አይሁን። ፈውሰኞች ይጠየቁ፤ ይፈተሹ። ሕሙማኑ አብረዋቸው የሚከርሙትና የሚባጁት መጋቢዎችና መሪዎች በተለይ ጠያቂ መሆን አለባቸው። ሕመሙ አብሮአቸው የሚከርም ሕሙማንም ጠያቂዎች መሆን አለባቸው። ይህ እምነት ማጣት አይደለም። ራስን ያለማሞኘት ነው እንጂ።

ከላይ በጠቀስኩት ከኤድስ እንደተፈወሰ የተነገረበት ሰው ያለበትን ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ስለነገሩ እውነትነት ስጠይቀው "እውነት ነው" አለኝ። እንዴት እንዳረጋገጠ ስጠይቀው ግን የተነገረውን ከማመን በቀር አላረጋገጠም። ምክንያቱን ስጠይቀው ከባህላችን ምስጢረኛነት የተነሣ አንዳንድ ጉዳዮች ወደ አደባባይ እንደማይወጡ ነገረኝ። ይህ የዚያ ሰው መጋቢ ነው። እንደተረዳሁት ለማረጋገጥ ፈቃደኛ ያልሆነው ከተፈዋሹ ይልቅ ለፈውሰኛው ጥንቃቄ ሲል ነው።

ማሔስ ቀላል አይደለም፤ ግዴታ ለሚሰማቸው ብቻ እንጂ የሚጥም አይደለም። ማሔስ ማስጠንቀቅ ነው። ማሔስ ከኖረ ስሕተት አለ ማለት ነው። ሒስ ሲደረግ መበርገግም፥ መሸሽም፥ በክስ ዶሴ መምጣም፥ ማስፈራራትና መዛትም፥ በሥጋ መገለጥም መኖራቸው እውነት ነው። እነዚህ ግን ይህን የማሔስ ልምድ ከመንገድ ሊያስወግዱት የተገባ አይደለም።

በርካታ ጠያቂዎች መነሣታቸው መልካም ነው። የምካቴ ክርስትና (ዐቃቤ እምነት) ሰዎች መነሣታቸው፥ መጠየቃቸው፥ ማስተማራቸው፥ መስበካቸው፥ መጻፋቸው መልካም ነው። ይህ ቀጣይ እንዲሆን መበረታታትም አለባቸው። መለመድ እንጂ ማስደንገጥ የለበትም። የተሳሳቱ ልምምዶችንና ትምህርቶችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያዘምቱ ሰዎች የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል አይደለምና እንደ ዘበት መታለፍ የለበትም። 'ፈጣን ሎተሪ' እንደሚሉት ያለ ወዲያው ተጭሮ እንደሚያገኙት ባለ ቁማር ውስጥ ገብተው ለማያረካ ሕይወት የተዳረጉ ክርስቲያኖች ቁጥርም የዋዛ አይደለም። ክርስትና ክርስቶስን መምሰል እንጂ ብዙ ጊዜ ተበልተን አንዴ የምንበላው ቶምቦላ አይደለም። የሐሰት ትምህርቶችና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አፍንጫችን ተይዞ የምንጋታቸው የስሕተት ልምምዶች ዛሬም አያሌ ናቸው። እና ለምን እንደማሔስ ተረዱልኝ።

ጌታ ከአርያም ይባርካችሁ።

ዘላለም መንግሥቱ © 2014 (፪ሺህ፯) ዕዝራ ስነ ጽሑፍ አገልግሎት


Recommended